‹‹ቫይበር፣ ዋትስ አፕና ዊቻትን የመሳሰሉት ደርምሰውን ገብተዋል››- ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ

ባህርዳር፡ጥር የካቲት 1 /2010 ዓ/ም(አብመድ)በቢዝነስ አስተዳደር ሶስተኛ (ፒ ኤች ዲ) ዲግሪ ይዘዋል፡፡ ለ17 ዓመታት በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች አስተምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ-ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ፡፡ 
ሁሉንም የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በሞባይል አገልግሎት ማዳረስ ተችሏል? የኢተርኔትና የሞባይል አገልግሎት ሆን ተብሎ እንዲቋረጥ ይደረጋል ይባላል? ተቋሙ በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተሸላሚ መሆኑ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ሲነፃጻር እንዴት ይገለፃል? በዘርፉ ፈተናዎችና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከዶክተር አንዷለም ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡፡
Image may contain: 1 person, standing

አዲስ ዘመን፡ -ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን የተቀላጠፈና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ምን ምን ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ኢትዮ ቴሌኮም ከተመሰረተ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ተቋም ነው፡፡ የዕድሜውን ያህል ኢንቨስት ተደርጎበታል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ኢንቨስትመንቶቹ የዛሬ 10 ዓመት ነው ዘግይተው የተጀመሩት፡፡ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ተደርጎ የሞባይል አገልግሎት የማስፋፊያ ስራ ተካሄደ፡፡ይህም የሞባይል አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረበት ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት መንግስት ለትምህርት፣ ለግብርናና ለጤና ትኩረት ሰጥቶ ኢንቨስት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ኢንዱስትሪውና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነው መሄድ ያለብን በሚል አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ለማዘመን ደግሞ ወደ ኋላ ሲንቀራፈፍ የነበረውን ቴሌኮም የማዘመን ስራ መቅደም አለበት፡፡በዚህ ጊዜ የነበረው የኔት ወርክ ቴክኖሎጂ አቅም ከአገሪቱ ዕድገት ጋር መራመድ ተሳነው፡፡ ብዙ ፋብሪካዎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ተቋማት የሚፈልጉትን የቴሌኮም አገልግሎት ማቅረብ አልቻለም፡፡ እናም ተቋሙ ፈርሶ አዲስ ተቋም ይቋቋም ወይንስ ያለውን እየጠገንን እንሂድ የሚሉ አስተሳሰቦች ተነሱ፡፡

በሀሳቦች ፍጭት አፍርሶ መገንባት የሚለው የበላይነት በማግኘቱ እኤአ በ2010 ፍራንስ ቴሌኮም በ30 ሚሊዮን ዩሮ ማኔጅመንቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ኩባንያው የተቋሙን የውስጥ አደረጃጀት በመቀየር ከወረቀት ነጻ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመፍጠር ሊያዘምነው ችሏል፡፡

ከመሰረተ ልማት አኳያም ከአስር ዓመት በፊት የተገነባው የቴሌኮም መሰረተ ልማት የኔት ወርክ አቅም እያደገ የመጣውን የተጠቃሚውን ቁጥር ሊሸከም አልቻለም፡፡ የሚሸከመውም ከ20 ሚሊዮን ያልበለጠ ደንበኛ ነበር፡፡ይህንን አቅም ለማጎልበት ከሶስት ዓመት በፊት በአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የቴሌ ኮም መሰረተ ልማት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ተደረገ፡፡

አገሪቱን በ13 የቴሌኮም ሰርክሎች በመክፈል ለሶስት የተለያዩ ኩባንያዎች ተሰጥቶ የማስፋፊያው ስራ መካሄድ ጀመረ፡፡ በዚህም ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ማለትም የሁለተኛው ትውልድ(2ጂ)፣የሶስተኛው ትውልድ(3ጂ)፣አራተኛው ትውልድ(4ጂ) የቴሌ ኮም አገልግሎት የሚሰጡ ማስፋፊያዎች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ 4ጂ ላይ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ናቸው ኢንቨስት ያደረጉት፡፡ ከኢንፎርሜሽን ስርዓትም ዘመናዊ የተባለው ነው የተዘረጋው፡፡ እናም እያየንና እያጠናን ደንበኞች የሚፈልጉትን ምርቶችና አገልግሎቶች እያቀረብን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በሞባይል አገልግሎት ማዳረስ ተችሏል?

ዶክተር አንዱዓለም፡- አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ 85 በመቶ የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በኔት ወርክ መሸፈን ተችሏል፡፡ ሆኖም የኔት ወርክ ችግር በሚታይባቸው ቦታዎች የዛሬ ስድስት ዓመት ዲዛይኑ ሲሰራ ህብረተሰብ ያልሰፈረባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ አካባቢ የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ ኔት ወርኩ ተጨናንቆ የሚፈለገውን አገልግሎት በጥራት የማይሰጥበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

ከመልክዓ ምድራቸው አቀማመጥ የተነሳ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተቸገርንባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡፡ለምሳሌ ሰሜን ጎንደር ዞን ሄሊኮብተር ተጠቅመን ነው ታወሮችን ተራራ ላይ ማውጣት የቻልነው፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ካጋጠመ እንጂ በአጠቃላይ 85 በመቶ የአገሪቱ የቆዳ ሽፋን በ2ጂ ፣3ጂና 4ጂ ኔት ወርክ የተሸፈነ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳና ጠለምት ወረዳዎች የሞባይል አገልግሎት በከፊል እንደሚያገኙ ነዋሪዎች ቅሬታ አቅርበው ተቋማችሁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ችግሩን እንደሚፈታ ቃል ገብቶ ነበር፡፡አሁን ችግሩ ተፈትቷል?

ዶክተር አንዱዓለም፡- ገና አልተፈታም፡፡ የውጭ ምንዛሬ የማግኘቱ ሂደት በመራዘሙ ዕቃዎቹን በፍጥነት ከውጭ ገዝቶ ማስገባት አልተቻለም፡፡ አሁንም ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ለብቻው ነጥለን መፍትሔ ለመስጠት እየሞከርን ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ትልቁ ማነቆ የሆነብን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አሁንም ክፍተቱ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡-በአሁኑ ጊዜ ኢትዮ ቴሌኮም ምን ያህል ደንበኞች አሉት?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ከ62 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሞባይል፣ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ደግሞ የመስመር ስልክ ደንበኞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ደንበኞቻችን ከ63 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡-የኢንተርኔት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ምን ያህል ተደራሽ ነው?

ዶክተር አንዱዓለም፡-ውቅያኖስን አቋርጦ በጅቡቲ ፣በሱዳንና በኬንያ መግቢያ በሮች በኩል የሚመጣና ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ መሬት ውስጥ የተቀበረ (መስመር) ኬብል አለ፡፡ ስለዚህ መንገድና ህንጻ ሲገነባ መሬት ውስጥ የተቀበሩት ኬብሎች ከተቆረጡ አገልግሎቱም አብሮ ይቋረጣል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀበሩት ኬብሎች እርስ በርሳቸው እንዲጠላለፉ(እንዲገናኙ) ተደርጓል፡፡ አንዱ ቢቆረጥ በሌላው መስመር አገልግሎት መስጠት ይቻላል፤ለመጠገንም ጊዜ ይሰጣል፡፡ ወደ ክልሎች የተዘረጋው ግን አንድ መስመር በመሆኑ እሱ ከተቆረጠ አገልግሎቱም ይቋረጣል፡፡እነዚህ ችግሮች በአገልግሎታችን ላይ እክል ይፈጥራሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢተርኔትም ሆነ የሞባይል አገልግሎት ሆን ተብሎ እንዲቋረጥ ይደረጋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ይህ ምን ያህል እውነትነት አለው?

ዶክተር አንዱዓለም፡-ሆን ተብሎ ሊደረግ አይችልም፡፡ምክንያቱም እኛ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ነው ዋናው አለማችን፡፡ ግባችን ለደንበኞቻችን የተሻለ እርካታን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት በምንጥርበት ጊዜ አንድና ሁለት ሰራተኛ ከኩባንያው ዓላማ ውጭ ከተንቀሳቀሱ ተገቢነት የለውም፤ ኩባንያውንም አይወክሉም፡፡ ሆን ተብሎ የሚደረግ አይኖርም፡፡

አንዳንድ ድርጅቶች በራሳቸው አጠቃቀም ችግር ምክንያት አገልግሎት የማይሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለ10 ሺ ሰዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም ያለው ዋይፋይ 11ሺ ሰው የሚጠቀምበት ከሆነ ኔት ወርኩ ስለሚጨናነቅ መዘግየት ይፈጠራል፡፡ ይህ ከራስ አጠቃቀም ጋር ይያያዛል፡፡ 
አዲስ ዘመን፡- የጸጥታና የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚቋረጠው ለምንድን ነው?

ዶክተር አንዱዓለም፡-ኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት በመክፈትና በመዝጋት ሂደት ውስጥ አይገባም፡፡ መንግስት የራሱ አደረጃጀት አለው፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ አንጻር የማቋረጥ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡

አዲስ ዘመን፡-በዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ተሸላሚ ሆናችኋል፡፡ ይህ ሽልማት ከአገልግሎታችሁ አንጻር ተገቢነት አለው የሚል እምነት አለዎት?

ዶክተር አንዱዓለም፡-በአሁኑ ጊዜ ተቋሙ በፈጣን ዕድገት ላይ ነው፡፡ ከነበረበት የደንበኞች እሮሮና አቤቱታ ራሱን አላቋል፡፡ የደንበኞች ተጨማሪ አገልግሎት የመፈለግ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ አገልግሎቱ ከበፊቱ በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ከወረቀት ነጻ የሆነ ዘመናዊ ሥርዓት በመዘርጋት አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ አንድ የዓለም አቀፍ ተቋም ባጠናው ጥናት መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም በኔት ወርክ አቅሙና በግዝፈቱ ከአፍሪካ አንደኛ፤ በዓለም ደግሞ 31ኛ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የሰበሰበውን ገንዘብ ለአገር ልማት ነው የሚያውለው፡፡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲውል ነው የሚያደርገው፡፡ ሽልማቱ በፍጥነት ማደጋችንን፣ ዘመናዊ አሰራር መተግበራችንና ለማህበረሰቡ የምናደርጋቸውን አስተዋጽኦዎች ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው፡፡

ተቋሙ እስካሁን ድረስ በአስራዎች የሚቆጠሩ ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽልማቶች ተሰጥተውታል፡፡ ይህ ግን ኢትዮ ቴሌኮም የተጨበጨበለትና የደንበኞችን እርካታ ጥግ ያደረሰ ነው የሚል ትርጓሜ የሚያሰጥ አይደለም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ክፍተቶች አያጋጥሙም ብሎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ተቋማት አማካኝነት ለዘጠኝ ዙር ያህል የደንበኞች እርካታ ጥናት ተካሄዷል፡፡ በክልሎችም ሆነ በአዲስ አበባ ደንበኞች በተቋሙ አገልግሎት ጥሩ እርካታ እንዳላቸው ነው ጥናቱ የሚያመላክተው፡፡ እርካታውን ለማሳደግ አሁንም ብዙ መስራት አለብን፡፡

አዲስ ዘመን፡-ኢትዮ ቴሌኮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ አቻ ኩባንያዎች ጋር የመወዳደር ብቃት አለው ብለው ያምናሉ?

ዶክተር አንዱዓለም፡- በአሁኑ ጊዜ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ለመወዳደር የሚያስችለው አቅም፣ አደረጃጀትና የሰው ኃይል እንዳለው በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ አገልግሎቱን ከአገር ውጭ ለመስጠት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በየትኛው በኩል ብንገባ ተወዳዳሪ እንሆናለን በሚል የጎረቤት አገሮችን ደካማና ጠንካራ ጎን እያጠናን ነው፡፡

መንግስት ለቴሌኮም መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ያደረገው አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡ ውድድር ቢኖር እንኳ ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ልክ ተዘጋጅቷል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ከአገር ውጭ ኢንቨስት ለማድረግ ዓለም አቀፍ የንግድ ክፍል አቋቁመናል፡፡ ለመወዳደር የሚያስችል አደረጃጀትና ተቋም ፈጥረናል፡፡ በተከታታይ ሰራተኞቻችን የምናሰለጥንበት የቴሌኮም ማሰልጠኛ አካዳሚ አለን፡፡ለሁሉም ተማሪዎች ክፍት ከመሆኑም በላይ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች የሚመጡም የሚሰለጥኑበት ነው፡፡ ተወዳድረን ለማሸነፍ የምንችልበት አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል አቅምና ቴክኖሎጂ እየፈጠርን ነው፡፡እኛ አገር አገልግሎቱን ብቻችንን የምንሰጥ ቢሆንም ከአቻ ተቋማት ጋር እየተወዳደርን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ እነ ቫይበር፣ ዋትስ አፕና ዊቻትን የመሳሰሉት ደርምሰውን ገብተዋል፡፡ እዚህ ገብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ በድርድርም ሆነ በቴክኖሎጂ ከእነሱ በልጠን ገቢ መካፈል አለብን፡፡ ግማሹ እየሰረቀን ግማሹ ደግሞ በቴክኖሎጂ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ እየመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማችን ተወዳዳሪ መሆን ይችላል፡፡ የእኛ መሀንዲሶች አውሮፓና አሜሪካ እየሄዱ ነው የሚሰሩት፡፡

አዲስ ዘመን፡-ኢትዮ ቴሌኮምና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ተናበው ባለመስራታቸው በተለይም የእግረኛ መንገዶች በየጊዜው ሲቆፈሩ ይስተዋላል፡፡ በዚህም የአገር ሀብት ከመባከኑም በላይ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ እየገቡ ህይወታቸው የሚያልፍበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

ዶክተር አንዱዓለም፡-ይህ ችግር መስተዋሉ እውነት ነው፡፡ እኛም እንደ ተቋም የሚያሳስበንና የሚቆጨን ጉዳይ ነው፡፡ በጋራ አቅዶና ተቀናጅቶ ብዙ ገንዘብ ማዳን ሲቻል ሁሉም በራሱ መንገድ ሲጓዝ፤ አንዱ በጀት ሳይፈቀድለት ወደ ኋላ ሲጎተት፤ ሌላው የቆፈረውን መልሶ ሲቆፍረው ጉድጓዱ ሳይከደን ቀርቶ የሰው ህይወት ሲጠፋ ማየት ያሳዝናል፡፡

አሁን መሰረተ ልማቶችን የሚያቀናጅ ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃና ፍሳሽ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ባቡር ኮርፖሬሽን ተቀናጅተን እንድንሰራ የሚያስችል ነው፡፡ አሁን ሁሉም በየፊናው መቆፈር አይችልም፡፡ ለምሳሌ አሁን እኛ መንገዶች ካልፈቀደልን እንደፈለግን መንገድ መቁረጥ አንችልም፡፡ መንገድ ሲሰራ በጀት እንሰጥና የእኛም ስራ አብሮ ይሰራል፡፡ ከበፊቱ ብዙ ለውጥ ቢኖርም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ግን አልተደረሰም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ባለፉት ስድስት ወራት ኢትዮ ቴሌኮም ምን ያህል ገቢ አገኘ?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ባለፉት ስድስት ወራት ዕቅዳችን 19 ቢሊዮን ብር ቢሆንም 18 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለናል፡፡የዓመቱ ዕቅዳችን 38 ቢሊዮን ብር ሲሆን ዕቅዱን ለማሳካት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?

ዶክተር አንዱዓለም፡- ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ የቴሌ ኮም ማጭበርበር ትልቁ ፈተና ሆኖብናል፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመጣመር እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ እያስገኝ ያለ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ነው የሚሻሙብን፡፡ ስለዚህ የመቆጣጠር ስራ ብንሰራም የቴሌኮም ማጭበርበር አሁንም ፈተናችን ስለሆነ በተከታታይነት መስራት አለብን ፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ በመሰረተ ልማቶቻችን ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው፡፡ ከስምንት ሺ በላይ ታዎሮች አሉን፡፡ መሬት ላይ የተቀበረ ፋይበር ኬብል አለ፡፡ ይህን ሆን ብለው ወይም ሳያውቁ የሚቆርጡ አሉ፡፡ለመጠገንም ጊዜ ይወስዳል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ሌላው ፈተናችን ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከ80 በመቶና በክልሎች ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ መጠባበቂያ ጄኔሬተሮች አሉን፡፡ ለጄኔሬተሮች ነዳጅ ለመሙላትና ለጥገና ብዙ ወጪ ያስፈልጋል፡፡ ጄኔሬተሮቹ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ አገልግሎቱን እንዳይቋረጥ ወሳኝ ናቸው፡፡

በዓለም ላይ ቴክኖሎጂው እየተለዋወጠ መምጣቱን ተከትሎ ቴሌኮም ገቢውን በከፍተኛ ደረጃ እያጣ ነው፡፡ አሁን ወደ አምስተኛው ትውልድ እየሄደ ነው፡፡አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት ካልተቻለ በዘልማዳዊ ቴሌኮም መምራት አይቻልም፡፡ ዛሬ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ደርምሰው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ እናም ኢንዱስትሪው የቴክኖሎጂ ፈተና አለበት፡፡ በሌላ በኩልም የግዥው ጉዳይ በውጭ ምንዛሬ ምክንያት ፈተና ሆኖብናል፡፡ አንዳንድ ግዥዎቻችን ቆመዋል፡፡ ችግሩ ጊዜያዊ ቢሆንም ትልቅ ፈተና ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡-የሞባይል ስልክ ታሪፍ ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ?
ዶክተር አንዱዓለም፡- በዚህ ሀሳብ አልስማማም፡፡ በሞባይል ስልክ የዳታና የድምፅ አገልግሎት ነው የምንሰጠው፡፡ የድምፅ ታሪፍ ዋጋው ከምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛው ነው፡፡የዳታውም ቢሆን ከፍተኛ የሚባል አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡-ለ2ጂና ለ4ጂ የሚከፈለው ዋጋ ተመሳሳይ ነው?

ዶክተር አንዱዓለም፡- የዋጋ ልዩነት የላቸውም፡፡ 4ጂ እጅግ በጣም ፈጣን ነው፡፡ የሚከፈለው በወረደው ዳታ ልክ ነው፡፡ በ2ጂ መረጃ ለማውረድ የሚደረገው ጥረት ቀርፋፋ ነው፡፡ 2ጂ ሁለት ደቂቃ ሲወስድ 4ጂ 10 ሰከንድ ሲፈጅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጊዜን ይቆጥባል፡፡ ሁለቱም ግን ተመሳሳይ መፅሀፍ ነው ያወረዱት፡፡ ነገር ግን ሰው ጊዜና ዳታውን ሳይሆን ቆይታውንና ገንዘቡን ብቻ ነው የሚለካው፡፡

አዲስ ዘመን፡-የኢትዮ ቴሌኮም ቀጣይ ዕቅድ ምንድን ነው?

ዶክተር አንዱዓለም፡-ከአገር ውጭ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ ይዘናል፡፡ማስፋፊያ ካደረግን ስምንት ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ ጥናት በማካሄድ ማሻሻያዎች ለማድረግም ሀሳቡ አለ፡፡ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የማስፋፊያ መርሀ ግብርም ይኖረናል፡፡ በእነዚህ ማስፋፊያዎች ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
እስካሁን የተሰራው ሰውና ሰውን በስልክ ማገናኘት ነው፡፡ አሁን ግን ዓለም ሰውና ዕቃን፣ ዕቃና ዕቃን ማገኛነትን ነው እየሰራ ያለው፡፡ ለምሳሌ ቢሮ ሆነህ ቤትህ ላለ ዕቃ ደውለህ መልስ ይሰጥሀል፡፡ ፍሪጅህ ጋ ደውለህ ስንት እንቁላል ውስጡ እንዳለ ይነግርሀል፡፡ ይህን አገልግሎት የመስጠት ሀሳቡ አለን፡፡

በእኛ አገር አብዛኛው ህብረተሰብ ስልኩን ለመደወል፣ ኢሜልና መልዕክት ለመላላክ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ከዚህ የዘለለ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በመዝናኛ ዘርፍም አገልግሎት መስጠት ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አንዱዓለም፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ምንጭ፡-አዲስ ዘመን

 

 

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3693132
  • Unique Visitors: 209286
  • Published Nodes: 2809
  • Since: 03/23/2016 - 08:03