ትኩረት የተነፈገው ገዳይ!!

ባህርዳር፡ጥር 24/2010 ዓ/ም(አብመድ)አቶ ዘውዱ በዛ ይባላሉ፡፡የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡በግንባታ ስራ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ፡፡Image may contain: 1 person, closeup

በጥምቀት በአል ላይ ካጯት ባለቤታቸው ጋር ለ17 አመታት በጋራ ኖረዋል፡፡ሶስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡በነዚህ ሁሉ ዓመታት በፍቅር ተነፋፍቀው የሚኖሩ ባለትዳሮች ነበሩ፡፡በተለይ የልጆቻቸው እናት መልካም አሳቢና ተቆርቋሪ ነበረች፡፡

በቅርቡ አቶ ዘውዱ አገር አማን ብለው ቤተሰቦቻቸውን ተሰናብተው ከቤት ይወጣሉ፡፡ባለቤታቸውም እግራችውን ተከትለው የሁለት ዓመት ከሁለት ወር ልጃቸውን አዝለው ካሰቡበት ለመድረስ ከቤት ወጡ፡፡
ደብረታቦር ከተማ ‹‹አፋፍ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደረሱ፡፡ አስፓልቱን ለማቋረጥ መንገድ ዳር ቆሙ፡፡
በቅፅበት አንድ ተሸከርካሪ ከመሃል መንገድ ወጥቶ ወደ እናትና ልጅ ተምዘገዘገ፡፡ከፊትለፊቱ የገባውን ተሽከርካሪ አድናለሁ ብሎ ከዋና መንገድ የወጣው አሽከርካሪ እናትና ልጅ ላይ አደጋ አደረሰ፡፡
ጠረኗን ያልጠገቧት ልጃቸው ወዲያውኑ ህይወቷ አለፈ፡፡እናት ወደ ህክምና ተቋም ቢደርሱም መትረፍ አልቻሉም፡፡

አቶ ዘውዱም በሀዘኑ እጅግ ልባቸው ተሰበረ፡፡የባለቤታቸውና የልጃቸው አሟሟት ከውስጣቸው አልጠፋም፡፡
ልክ እንደ አቶ ዘውዱ ቤተሰቦች ሁሉ በትራፊክ አደጋ በየእለቱ በርካታ ዜጎች በወጡበት እየቀሩ ነው፡፡
Image may contain: plant, outdoor and nature

ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባገኘነው መረጃ መሰረት በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የትራፊክ አደጋ ጨምሯል፡፡ከአንድ ሺ አራት መቶ በላይ አደጋዎችም ተከስተዋል፡፡በእነዚህ አደጋዎች ደግሞ አራት መቶ አርባ አራት (444) ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እንደ ክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት የግንዛቤና ትምህርት ስልጠና ባለሞያ አቶ ይበልጣል ታደሰ መሰረት ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአደጋው ቁጥር በ57 ጨምሯል፡፡

በተጨማሪም አንድ ሺ አምስት መቶ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ከሃምሳ አንድ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል ብለዋል፡፡
አቶ ይበልጣል እንደሚሉት ከሆነ ቢሮው ከዚህ በፊት ባካሄደው ጥናተ መሰረት በክልሉ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 81 በመቶው በአሽከርካሪዎች ችግር የሚከሰት ነው፡፡

አሽከርካሪዎች ከተወሰነላቸው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርና የብቃት ማነስ የአደጋዎቹ መንስኤ ናቸው ሲል ጥናቱ ማስቀመጡን ገልፀዋል፡፡
ጥናቱ ይህን ይበል እንጂ ሌሎች ተጫማሪ ምክንያቶች በአደጋ መንስኤነት ይጠቀሳሉ፡፡ይህም ቢሆን እግረኞች ራሳቸውን ጠብቀው በመጓዝና አሽከርካሪዎችም አደጋን ተከላክሎ በማሽከርከር የራሳቸውንና የወገናቸውን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የስድስት ወራት ሪፖርት መሰረት እድሚያቸው ከ18 እስከ 30 የሆኑ አሽከርካሪችዎች 56 በመቶ አደጋ በማድረስ ቀዳሚ ናቸው፡፡በመቀጠል ደግሞ ከ31 እስከ 50 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አሽከርካሪዎች አደጋ ፈፃሚዎች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

የችግሩ ገፈት ቀማሽ አቶ ዘውዱ በዛ ‹‹የቁጥጥር ማነስ፣የግንዛቤ ፈጠራ እንዲሁም የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚመለከተው አካል ትኩረት በማድረግ በእያንዳንዱ ቤት እየደረሰ ያለውን አደጋ መታደግ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በሰራናቸው መሰናዶዎች መሰረት ለትራፊክ አደጋ መባባስ የማሰልጠኛ ተቋማት አሰራር ችግር፣ የግንዛቤ ክፍተትና የቁጥጥር መላላት እጃቸው እንዳለበት አረጋግጠናል፡፡
ችግሩም ትኩረት የተነፈገው ገዳይ ሆኖ ህዝቡ ላይ በየእለቱ የማይሽር ጠባሳ እያደረሰ ነው፡፡
በሀናንያ አዘነ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3693121
  • Unique Visitors: 209285
  • Published Nodes: 2809
  • Since: 03/23/2016 - 08:03