ግብጽ ሸማቂዎችን ትረዳለች በሚል ሱዳን ወቀሰች

ባህር ዳር፡ ግንቦት 17/2009 ዓ/ም(አብመድ)ግብጽ ከካርቱም መንግስት ጋር እየተዋጉ ያሉ ሸማቂዎችን ትረዳለች በሚል የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል ባሽር መውቀሳቸውን ሮይተርስ ዘገበ ፡፡

በሁለቱ ጎረቤት ሃገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር በቀጣዩ ሳምንት ወደካይሮ ለመጓዝ ቀጠሮ በያዙበት ባሁኑ ሰዓት የሱዳን ጦር ሃይል ጦርነት ከማይለያት ደቡባዊ ዳርፉር ግዛት ሸማቂዎች ላይ ግብጽ ያስታጠቀቻቸውን ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች መማረኩን አል ባሽር ተናግረዋል ፡፡

ግብጽና ሱዳን ከቅርብ ወራት ወዲህ በመሬት ይገባኛል ውዝግብ ፣ በንግድ ቁጥጥር እና በቪሳ አጠቃቀም ዙሪያ አለመግባባቶች በመፍጠራቸው የሁለትዮሽ የገበያ ትስስሩ አደጋ ላይ መውደቁ እየተነገረ ነው ፡፡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወቀሳውን በማስተባበል ‹‹ ግብጽ የሱዳንን ሉአላዊነት የምታከብር በመሆኗ ለአንድም ቀን ቢሆን ጣልቃ ገብታም ሆነ የሱዳንን ህዝብ የሚጎዳ ተግባር ፈጽማ አታውቅም የመፈጸምም ፍላጎት የላትም ›› ብለዋል ፡፡ በዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚፈለጉት ኦማር አል ባሽር በደቡባዊ ሱዳን ከሚገኙ ሶስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር ለዓመታት በውጊያ ውስጥ መቆየታቸው ይታወቃል ፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537605
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03