የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በቻይና ያካሄደው ጉብኝት ስኬታማ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

ባህር ዳር፡ ግንቦት 14/2009 ዓ/ም(አብመድ)የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በቻይና ያደረገው ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ታላቅ ደረጃ ላይ በማድረስ ስኬታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስርት ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በተቀናጀ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ደረጃ ላይ የደረሰች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ስትሆን፤ ይህም በቻይና የውጪ ግንኙነት ታላቅ ደረጃ የሚባል ነው።

"በኢትዮጵያና በቻይና መካከል እና በህዝቦቻቸው መካከል ያለው ግንኙነት የመጨረሻው የከፍታ ደረጃ እንዲደርስ ተደርጓል። በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ነው ተብሎ ይወሰዳል"  ብለዋል።

ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ለሚኖራት የልማት ተሳትፎ እንደበር ከምታያት ኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግና ለማጠናከር እየሰራች ነው። ይህም ቻይና የ"ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭን" ጨምሮ በአፍሪካ ለምታካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ እንደዋነኛ መነሻ  አድርጋ እንድትመርጣት አስችሏታል።

ለዚህም ነው በቤጂንግ ከግንቦት 6 እስከ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ በቆየው የ"ቤልት ኤንድ ሮድ" መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከአፍሪካ ከተመረጡት ሁለት አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ በመድረኩ ላይ የተደረሰው የጋራ መግባባት ልዩ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በሲኖ-አፍሪካ ግንኙነትም ሆነ "ሲልክ ኤንድ ቤልት ሮድ" ልማት ማዕቀፍ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ለማነሳሳት የሚያስችልም ነው።

"ከዚህ በፊት በትብብር ማዕቀፎች ውስጥ አንደኛው ተረጂ ሌላኛው ረጂ በሚመስል መንገድና እርዳታና ብድር ለመስጠት ግን ታዳጊ አገሮች የፖሊሲ ኪራይ ለመስጠት የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። የእያንዳንዱ አገር ፖሊሲ የማውጣት፣ ፖሊሲ የመተግበር ነጻነት መጠበቅ አለበት በሚል ጉዳይ ላይ ስምምነት ተደርሷል። ይሄ እንግዲህ ከሌሎቹ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተለየ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የአገሪቷን አጠቃላይ እምቅ አቅም በማስተዋወቅ የቻይናን ታላላቅ ኩባንያዎች ለመሳብ እድሉን ተጠቅመውበታል። ልዑካኑ አራት የቻይና ዋናኛ ግዛቶችን ጎብኝቷል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጻ፤ በሻንዶንግ፣ ፉጃን፣ ሁናን እና ሺቹዋን ያደረጉት ጉብኝት የተሳካ ነበር።

የልዑካን ቡድኑ በጉብኙቱ ወቅት ከታላላቅ ኩባንያዎቹና ከግዛቶቹ መሪዎች ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የአገሪቷን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውጤት፣ የኢንቨስትመንት እድሎችና ድባቡን ለመግለጽ ችለዋል።

"ዋና ዋና ኩባንያዎቻቸውን ለማግኘት ችለናል። አስረድተናል። አብዛኛዎቹ ደግሞ በአገራችን ኢንቨስት ለማድረግ ወስነዋል። ከሁሉ በላይ ግን ጥሩ ውጤት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው እያንዳንዱ የቻይና ክፍለአገሮች አሁን የጎበኘናቸው አራቱም ክፍለአገሮች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የኢንዱስትሪ ዞን መንግሥታቸው እንደሚያደራጅና ባለሀብቶቻቸው ባደራጁት በራሳቸው ኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ እንደሚገቡ ቃል ገብተውልናል" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

በሁለትዮሽ ግንኙነት ወቅት የግዛቶቹ መሪዎች ታላላቆቹ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ እንደሚያበረታቷቸው መግባባት ላይ ተደርሷል።

ምንጭ፡ኢዜአ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3406100
  • Unique Visitors: 192814
  • Published Nodes: 2592
  • Since: 03/23/2016 - 08:03