የአማራ ክልል ሲቪል ስርቪስ የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከወረዳ ና ከዞኖች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡

ባህር ዳር፡ ግንቦት 16/2009 ዓ/ም(አብመድ)ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት አስተያየታቸውን የሰጡት ተገልጋዮች እንዳሉት አንድ እርከን ዝቅ በተባለ ቁጥር አገልግሎት አሰጣጡ እየቀነሰ እንደሚመጣ ገልጸው የተገልጋዮች መንገላታት በአስቸኳይ ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡ 


አቶ ምናለ በዛብህ እንደሚሉት የሲቪል ስርቪስ ፍርድ ቤት(ማህበራዊ ፍርድ ቤት) በግል ጉዳይ በመጡበት ወቅት አንድ ዳኛ አስደንግጦኝ ነበር ካሉ በኋላ አሁን ግን ጉዳዩን በጥሩ አክብሮት እና መስተንግዶ ፈጽመውልኛል ሲሉ በአገልግሎቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ 


አቶ አብርሃም ተስፋው የተባለ ተገልጋይ በበኩሉ እንዳለው አስተዳደር ፍርድቤቱ ላይ ያለው አገልግሎት ፈጣን እና ቀልጣፋ ከመሆኑም በተጨማሪ ጉዳያችንን በመረዳት በኩል እየሰሩ ነው ብሏል፡፡


አቶ ዮሃንስ አሰፋ በበኩሉ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ጉዳዩ መታየቱን አስታውሶ ጉዳየን ላስፈጽም ስንቀሳቀስ አንድ ሰው ለማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ወደየት በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለብን የሚገልጽ መግለጫ የላቸውም ፡፡የሉም ቆይተህ ተመለስ ወይንም ሌላ ቀን ና በሚል ብዙ ሲያጉላሉኝ ቆይተዋል ካለ በኋላ የአማራ ክልል ሲቪል ስርቪስ የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ማህበራዊ ፍርድ ቤት ስመጣ ግን ጉዳይ ተቀባዮች ወደምፈልገው ቦታ ስላደረሱኝ እና ክፍሉም በሚገባ ተቀብሎ አስተናገደኝ ጉዳየን ፈጽሜአለው ብሏል፡፡ 


የአማራ ክልል ሲቪል ስርቪስ የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገለታ ስዩም እንዳሉት በሁሉም መስራቤቶች ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የአሰራር ማሻሻያዎችን ሰርተን ወደታች ለማውረድ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ 
እንደ ሃላፊው ገለጻ ብዙዎቹን መመሪያዎች የማስተካከል ስራ ነው የሰራነው አንዳንዶቹን አጠናቀናል ፡፡አንዳንዶቹን መመሪያዎች ደግሞ በድራፍት ደረጃ ተቀምጠው እየተወያየንባቸው ነው፡፡


ከተሃድሶ በኋላ ከዞን እና ከከልል በመጡ ግምገማዎች መሰረት ለማስተካከል እየሞከርን ቢሆንም በቂ ግን አይደለም ሲሉ ተገልጋዮች ላነሱት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ 
የአገልጋይነትን መንፈስ ለመፍጠር የአንድ ሰሞን የተሃድሶ ንቅናቄ ብቻ በቂ አይደለም የሚሉት አቶ ገለታ ስዩም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚፈጠሩ ችግሮች በመሆናቸው በቂ ስልጠና ለመስጠት እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡ 


የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱት በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን ተገልጋዩ ከአዋጆች ከደንቦች እና ከመመሪያዎች አንጻር መብቱ እና ግዴታውን አውቆ ሊመጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ክልሉ በበጀት አመቱ 92 ሚሊየን ብር በመበጀት 15 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ መንግስት ሰራተኝነት እንዲቀላቀሉ መደረጉን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አወቀ ካሴ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537603
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03