የሱዳን ፕሬዝዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር ከአረብ መሪዎች ጉባኤ ላይ እንደማይገኙ ተናገሩ

ባህር ዳር፡ ግንቦት 11/2009 ዓ/ም(አብመድ)በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) የሚፈለጉት የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በሚሳተፉበት የሳውዲ አረቢያ የአረብ መሪዎች ጉባኤ ላይ እንደማይገኙ ማስታወቃቸው ግርምት መፍጠሩን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
 
ሪያድ ውስጥ በሚከናወነው የአረብ መሪዎች ጉባኤ ላይ በመገኘት ከዋሽንግተን ለሚነሳው ጠንካራ ትችት ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ አለመገኘታቸው ቢያስገርምም የሳውዲ አረቢያን ንጉሥ ሳልማንን ግን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
 
ፕሬዝዳንት አልበሽር በዚህ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በተለይም ከትራምፕ ጋር በመነጋገር የሃገራቸውን ፖለቲካዊ ገጽታ መገንባት ሲገባቸው ለመቅረት መወሰናቸው ብዙዎቹን ግራ አጋብቷል፡፡
 
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ሱዳን ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያሳየችው ቁርጠኝነት ፤ከጎረቤት ሃገራት እና ከአለም መንግስታት ጋር ተባብሮ ለመስራት የያዘችው አቋም እያደገ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ በማስፈሩ የትራምፕ አስተዳደር ሙሉ በመሉ ማእቀቡን እንደሚያነሳ አመላካች ነው ተብሏል ፡፡
 
አሜሪካ በሱዳን ላይ ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል እ.ኤ አ. ከ1997 ጀምሮ ሰሞኑን አንዳንድ መሻሻል እስካደረገችበት ጊዜ ድረስ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥላባት ቆይታለች ፡፡
 
በቅርቡ ደግሞ ሱዳን ከኢራን ፣ ከኢራቅ፣ ከሊቢያ፣ከሶማሊያ፣ ከሶሪያ እና ከየመን ጋር ተቀላቅላ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው ሰባት ሃገራት ውስጥ መካተቷ የሚታወስ ነው፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537604
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03