የሞሮኮ ቀዳማዊ እመቤት ካንሰርን በመዋጋት ላደረጉት አስተዋኦ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኑ

ባህር ዳር፡ ግንቦት 18/2009 ዓ/ም(አብመድ)የሞሮኮ ቀዳማዊ እመቤት ልዕልት ላላ ሳልማ ካንሰርን ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ የመጀመሪያዋ ሴት በሚል በዓለም የጤና ድርጅት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆናቸውን ሲጂቲኤን ዘገበ ፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ልዕልት ላላ ሳልማ ካንሰርን ለመዋጋት ሞሮኮ ውስጥ በተደረገ ሃገርአቀፍ ዘመቻ ግንባር ቀደም ሆነው በተለያዩ መድረኮች በመገኘትና ህብረተሰቡን በማንቃት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለስኬት አብቅቷቸዋል ብሏል የአለም የጤና ድርጅት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ልእልቲቷ ሞሮኮ ውስጥ የካንስር መከላከያና መቆጣጠሪያ ፋውንዴሽን በማቋቋም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአገሪቱ የአለም የጤና ድርጅት አስተባባሪ ሙሃሙድ ፉቅሪ እጅ የወርቅ ሜዳሊያውን ተቀብለዋል፡፡

በቅርቡ ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡት የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር-ጄኔራል ማርጋሬት ቻን ለልዕልት ሳልማ በላኩት መልእክት ላይ በስልጣን ዘመናቸው ካዩአቸው ጠንካራ እና ለህብረተሰብ ጤና ከሚተጉ ጠንካራ ሴቶች መካከል አንዷ እንደሆኑ ተናግረው ይህን መልካም ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡-ሲጂቲኤን

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3161856
  • Unique Visitors: 186711
  • Published Nodes: 2579
  • Since: 03/23/2016 - 08:03