የሚንስትሮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ጅቡቲ ማጓጓዝ የሚያስችል ቧንቧ ዝርጋታ ስምምነት እንዲፈረም ወሰነ

ባህር ዳር፡ ሰኔ 10 /2009 ዓ/ም(አብመድ)

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በሁለት የስምምነት ፍቃዶችና በሶስት አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ በመባል የሚታወቁትን የጋዝ ልማት ስፍራዎች ቀደም ሲል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ጅቡቲ ወደብ ማጓጓዝ የሚያስችል ቧንቧ ለመዘርጋት መብት የሚያሰጠው ስምምነት እንዲፈረም ወስኗል።

ስምምነቱ የሚፈረመው ፖሊ.ጂሲ.ኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ሊሚትድ ከተባለውና በብሪትሽ ቨርጅን አይላንድስ ከተመሰረተው ኩባንያ ጋር ነው።

በተመሳሳይ ዋይ.ኤም.ጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአነስተኛ የጽንሰ ወርቅ ማዕድን ማምረት ፍቃድ ላይም ከተወያያ በኋላ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ረገድ ጠቃሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ስምምነቱን እንዲፈረም ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማን ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም በአገሪቷ ኤሌክትሮኒክስ ንግድና በኢንፎርሜሽን ቴክናሎጂ የታገዙ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቀረበለት ረቂት አዋጅ ላይም ተወያይቷል።

ረቂቁ ምቹ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር፣ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ልውውጥን ህጋዊ እውቅና መስጠት፣ የተሳታፊዎችን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚደነግግ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክ መልእክት ልውውጥ ወቅት የተሳታፊዎችን ማንነት፣ የመልእክቶችን ትክክለኛነትና አለመካካድን በማረጋገጥ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ሕጉን ማውጣት እንዳስፈለገ ተገንዝቦ ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም ተመልክቷል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ ወዲህ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያጋጠሙትን የአሰራር ክፍተቶች ለመቅረፍና አገልግሎቱን የተሟላ ለማድረግ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004ን በማሻሻል ይጸድቅ ዘንድ ለምክር ቤቱ አስተላልፏል።

ስለ ዕፅዋት አዳቃይ መብት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም በመወያያት አንዳንድ ማስተካከያዎችን አክሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው መወሰኑን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3527300
  • Unique Visitors: 199328
  • Published Nodes: 2627
  • Since: 03/23/2016 - 08:03