በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር በመላ ሃገሪቱ ከ10 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ

ባህር ዳር፡ ሰኔ 10 /2009 ዓ/ም(አብመድ)

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ መርሃ ግብር በመላ ሃገሪቱ ከ10 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በ12 የስራ ዘርፎች እንደሚሳተፉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ

በ2015 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ብቻ በአሜሪካ ከ68 ሚሊየን በላይ ህዝብ በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ተሰማርቷል።

በዚህም በገንዘብ ሲሰላ ከ185 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጣ ስራ በበጎ ፈቃደኞች ተሰርቷል።

በኢትዮጵያም በተለይ ክረምት በገባ ጊዜ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች፥ ያለማስተጓጎል የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ይፈጽማሉ።

ታናናሾቻቸውን ከማስተማር እስከ ከተማ ፅዳት ድረስ ውድ የሆነ ግልጋሎትን መስጠት፥ ወጣቶች በክረምት የሚፈፅሙት ተግባር ነው።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚያስተባብረው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም፥ ዘንድሮ በመላ ሀገሪቱ ከ10 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር መንደፉን ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ጉዳይ ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተሩ አቶ ማቲያስ አሰፋ፥ መርሃ ግብሩ በሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚከናወን ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የትራፊክ ደንብ ማስከበር፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የከተማ ፅዳት እና ውበት እንዲሁም የማስተማር አገልግሎት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በዋናነት ይከናወናሉ ተብለው ከተለዩ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ክልሎችም በተመረጡት ተግባራት ወጣቶችን ለማሰማራት የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ወጣቶች፣ በአማራ ክልል 2 ነጥብ 7 ሚሊየን እንዲሁም በደቡብ ክልል 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ስራው ለማሳተፍ እቅድ መያዙም ተጠቅሷል።

የየክልሎቹ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችም አሁን ላይ ለበጎ ፈቃድ ስራ ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።

ወጣቶች በራሳቸው ፈቃድ በሚችሉት ዘርፍ ሁሉ ሃገራቸውን እንዲያገለግሉም ቢሮዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሁሉም ክልሎች እስከ ሃምሌ አጋማሽ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፥ ስራው ወጥነት ባለው መልኩ በወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ይመራል።

ባለፈው አመት በሃገራዊው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 12 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

ምንጭ፡- ፋና

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537550
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03