በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ በመቃወም የደቡብ አፍሪካ ወንዶች ሠልፍ ወጡ

ባህር ዳር፡ ግንቦት 13/2009 ዓ/ም(አብመድ)በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሴቶችና ህጻናት ስቃይና እንግልት በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘገበ ፡፡ በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ድብደባ ፣የወሲብ ጥቃትና ግድያን በጋራ የመከላከል ሃላፊነት ወንዶች መውሰድ እንዳለባቸው የሠላማዊ ሠልፉ አስተባባሪ ኮሎፌሎ ማሻ ተናግረዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ነጭ ቀሚስ በለበሰች ተሳታፊ በተመራው ሠላማዊ ሠልፍ ላይ በወንድ ጓደኞቻቸው የተገደሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ሥም ዝርዝር የያዙ ሠሌዳዎች ለህዝብ እይታ ቀርበዋል ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ወሲባዊ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ቀዳሚ ሃገራት መካከል ተጠቃሽ ስትሆን የፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 64 ሺ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ፡፡

በዚህ ጉዳይ የደቡብ አፍሪካውያን ዝምታ ሊያበቃ ይገባል የሚሉት የሰልፉ አስተባባሪ ማሻ ይህን አስነዋሪና ጨካኝ ተግባር በጋራ ልንዋጋው ይገባል ብለዋል ፡፡ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የመደፈር አደጋ ደርሶባት ህይወቷ ያለፈውን የአንዲት የ3 ዓመት ልጅ ቤተሰብን ለማጽናናት በተገኙበት ወቅት ሲናገሩ በዚህ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በአስቸኳይ ለፍርድ በማቅረብና ከዚህ በኋላ እንዳይደገም ሃገራዊና መንግስታዊ ሃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537567
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03