ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደሃገራቸው እየገቡ ነው

ባህር ዳር፡ ግንቦት 22 /2009 ዓ/ም(አብመድ) የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጉን ሊቀይር ይችላል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዝ እስካሁን ለመምጣት ፍላጎት ያላሳዩ ወንድም እና እህቶች ክብር እና መብታቸው ሳይደፈር ወደ ሃራቸው እንዲመለሱ ተመላሾቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሚነት የሱፍ ከዛሬ 6 ዓመት በፊት ያደገችበትን ኮምቦልቻ ከተማን ለቃ በህገወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ አረቢያ በማቅናት ከፖሊስ እየተደበቀች ተሳቃ ስትሠራ መቆየቷን ተናግራለች ፡፡
አሁን ግን የሳውዲ መንግስት የውጭ ዜጎች ሃገሩን ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን ትእዛዝ ተቀብላ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ወደ ሃገሯ መመለሷን ገልጻለች፡፡
አሚነት በመቀጠልም ሃገራችን በአሁኑ ሰዓት እያደገች በመሆኗ ሠርቶ መለወጥ ስለሚቻል በሰው ሃገር የቀሩት እህትና ወንድሞች ወደሃገራቸው ተመልሰው እዚሁ ቢሠሩ ጥሩ ይሆናል ብላለች፡፡
ሳውዲ አረቢያ ህገወጥ ዜጎች ከሃገሯ እንዲወጡ ከሰጠችው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ አንድ ሶስተኛው ቢገባደድም በሀገሪቱ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵውያን መካከል የተሰጠውን ዕድል ተጠቅመው ወደሃገራቸው የገቡት በጣም ጥቂት ናቸው ፡፡ 
እንደተመላሾች አገላለጽ በሳዑዲ ያለው ጫና በጣም የከፋ በመሆኑ የምህረት ጊዜው ካለፈ ሊከሰት የሚችለው ችግር ከሚታሰበው በላይ ሊሆን ይችላል ፡፡
ስለዚህ ጊዜ ሳያባክኑ ዜጎች ወደሃገራቸው ቢመለሱ ይበጃል ሲሉ አያይዘውም መንግስት ዜጎቹ እንዳይንገላቱ እያደረገ ያለውን ተግባር አድንቀው አሁንም ህጉ ሊቀየር ይችላል እያሉ የተቀመጡ ዜጎች ደጋግመው እንዲያስቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል ፡፡

 

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3161867
  • Unique Visitors: 186711
  • Published Nodes: 2579
  • Since: 03/23/2016 - 08:03