ሲኖዶሱ በመደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባው 14 የሚደርሱ ውሳኔዎችን አሳለፈ-በሳውዲ የሚገኙ ዜጎችም የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል

ባህር ዳር፡ ግንቦት 15/2009 ዓ/ም(አብመድ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው የዘንድሮው መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ 14 የሚደርሱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

          ብጹኣን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ እጩ ቆሞሳት ምርጫም የተደረገ ሲሆን በዓለ ሲመታቸውም ሐምሌ 9/2009 እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

         አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጰጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት በውሳኔዎች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው እንዳሉት በቤተክርስትያኒቱ የስርዓት ዘርፍ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉትን ማህበራውያን ተግባራት የዳሰሰ ለሀገራችንና ለቤተክርስትያናችን ሁለንተናዊ እድገት የሚበጀውን በማመቻቸች በሁሉም አቅጣጫ ያለው ህብረተሰብ የስራ ተነሰሽነቱን በበለጠ አጎልብቶ እንዲንቀሳቅስ የሚያስችል መልዕክት መሆኑን ምልአተ ጉባኤው ተመልክቶ ለተላለፈው አጠቃላይ መመሪያ ትኩረት ሰጥቶ በቀረበው አጀንዳ ከተወያየ በኋላ በርከት ያሉ ውሳኔዎች አሳልፏል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የራሷ የሆነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶሱ ካደመጠና ከተወያየ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለቋሚ ሲኖዶሱ መርቷል፡፡

ብጹዕ አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎችን በተመለከተ ሲኖዶሱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስ በመግለጫው አክለውም ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር 16 ለኢጲስ ቆፖስነት ተመርጠዋል፡፡ባዕለ ሲመታቸውም ሀምሌ 9/2009 ዓ/ም ቀን እንዲፈጸም  ተወስኗል፡፡

ሚያዝያ 10 ቀን በሚነበበው መጽሀፈ ስንክሳርና በፍትህ መንፈሳዊ መጽሀፍ ላይ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሾሙም የሚለው በ7ኛው መቶ አመት ግብጻውያን አባቶች በስርዋጽ ያገቡት ህገ-ወጥ ጽሁፍ ስለሆነ ምልአተ ጉባኤው ተነጋግሮ ጽሁፉ የሀገሪቱንና ቤተክርስትያኒያቱን ክብር የሚነካ ሆኖ በመገኘቱ ጽሁፉ እንዳይነበብና መጽሀፍቱም ውስጥ እንዲጠፋ ወደፊት በሚታተሙ መጽሀፎች እንዳይገባ ተወስኗልም ብለዋል ፡፡

ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተክርስትያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢሆንም ውሳኔው መከበር ስላልቻለ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለሆነ አሁንም በውሳኔው መሰረት የቅጥጥሩ ስርዓት ተጠናክሮ እነዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

ከቤተክርስትያኗ የዕምነት ስርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ያካሂዱ የነበሩ ያሏቸውን ግለሰቦችም እገዳ አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ መሠረት አሰግድ ሳህሉ የተባለ ግለሰብ ለበርካታ አመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሰራጭ በመኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመሆኑ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስም እንዳያስተምር ምዕመናንም እንዳይከተሉት ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ/ም ቃለ ውግዘት አስተላልፏል ብለዋል፡፡

የቤተክርስትያኗን መገናኛ ብዙሃን አቅም ለማጎልበትም 12 ሚሊዮን ተጨማሪ በጀት አጽድቋል፡፡በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስለ ዴር ሱልጣን ገዳም ችግርን በተመለከተ ሲኖዶሱ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝም ለኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢምባሲእና በኢትዮጵያ ለእስራኤል ኢምባሲና በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኢምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍ ተወስኗል፡፡

ሲኖዶሱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተነግሯል፡፡

በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሀገሩ መንግስት በሰጠው ቀነ ገደብ መሰረት ቀኑ ሳይደርስባቸው እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል ብለዋል ፓትሪያሪኩ

ጋሻው ፈንታሁን

ተጻፈ በመሠረት አስማረ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537587
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03