ምክር ቤቱ በአፋር ክልል አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ያቀረቡትን የልዩ ወረዳ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ባህር ዳር፡ ግንቦት 14/2009 ዓ/ም(አብመድ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ያቀረቡትን የልዩ ወረዳ ጥያቄ ውድቅ አደረገ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሔደ ይገኛል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2009 ዓ.ም ሪፖርት በኮሚቴው ሰብሳቢ በአቶ ወርቁ አዳሙ ቀርቦ አባላቱ በስፋት ውይይት አድርገውበታል።

በሪፖርቱ የማንነት መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ በአፋር ክልል ዞን ሁለት አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች "የማንነት መብታችን ቢከበርም ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችን ተሸራርፏል" የሚል ቅሬታ ለክልሉ ማቅረባቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ተወላጆቹ "ቋንቋችን፣ ባህላችንና ታሪካችንን የምናሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልንም" በማለት ጥያቄ እንዳቀረቡም ተመልክቷል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ጉዳዩን አጥንቶ አመልካቾቹ "ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የሌላቸው በመሆኑ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ነበር" ይላሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በክልሉ ውሳኔ ቅር በመሰኘታቸው ጉዳያቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል። ምክር ቤቱም ራሱን የቻለ አጥኚ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ ጉዳዩን ማስጠናቱን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል።

ቡድኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አናግሮና አካባቢውን ጎብኝቶ "ሁለቱም ብሔሮች በአካባቢው ተከባብረውና ተፋቅረው የሚኖሩ መሆናቸውን አረጋግጧል" ብለዋል።

በወረዳው የትኛውም የአገሪቷ አካባቢ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ለቀረበው የልዩ ወረዳ ጥያቄ አባባሽ ምክንያት መሆኑ "ታውቋል ነው" ያሉት።

በዚሁ መሠረት ''የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፣ ነገር ግን በአካባቢው የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታና ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች'' የሚል የውሳኔ ሀሳብ ከቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል።

የውሳኔ ሀሳቡን ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ተከትሎ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሓጅ ስዩም ''የክልሉ የስራ ቋንቋ አፋርኛ በመሆኑ ተወላጆቹ በአፋርኛ መማር አለባቸው'' ሲሉ ሞግተዋል።

ከዚህ ውጪ ያለውን የማህበራዊ አገልግሎቶች "ማንኛውም የአፋር ብሔር ተወላጅ እንደሚያገኘው ሁሉ እንዲያገኙ መብታቸው ይከበርላቸዋል" ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው "የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ያነሱት ሃሳብ 'ማንኛውም ህጻን በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር አለበት' የሚለውን ሕገ መንግስታዊ መብት ይንደዋል" ሲሉ ተቃውመውታል።

የደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች አቶ ደሴ ዳልኬና አቶ አብዲ ማሓመድ ኡመር "የቋንቋው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል" ብለዋል።

ክልሉ ይህን ቢያደርግ የሚጎዳው ነገር እንደሌለና የሚያጋጥም የበጀትና የግብዓት ችግር ካለ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል በኩል ቢያመቻች የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የደንጣ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄን የተመለከተ እስካሁን የተሰበሰበው መረጃ ለውሳኔ የሚያበቃ ባለመሆኑ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፏል።

ከዚህ ባለፈ በደቡብ ክልል የወለኔ፣ የቁጫ፣ የዶርዜ እና በኦሮሚያ ክልል የዛይና ጋሮ ማህበረሰብ ተወካዮች ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የማንነት ጥያቄ ወደ ክልሎቹ እንደሚለስ መደረጉም ተገልጿል።

ምክር ቤቱ እስካሁን ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ ውሳኔ የተሰጠባቸው አቤቱታዎች ተፈጻሚነት ጉዳይም ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።

ምክር ቤቱ በነገው እለትም የ2010 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገውን አዲሱን የክልሎች የድጎማና የበጀት ድልድል ተወያይቶ እንደሚያጽድቅ ይጠበቃል።

ምንጭ፡ኢዜአ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3870383
  • Unique Visitors: 214841
  • Published Nodes: 2859
  • Since: 03/23/2016 - 08:03