ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳንን ፆም ሲፆም የተራቡትን በማብላትና በመደገፍ መሆን አለበት፡-የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

ባህር ዳር፡ ግንቦት 17/2009 ዓ/ም(አብመድ)ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳን ፆም ሲፆም የተራቡትን በማብላትና በመደገፍ መሆን እንዳለበት የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አሳስቧል፡፡

ምክር ቤቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በመደገፍ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር መቆም እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የረመዳን ወርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ለአማራ ቴሌቪዥን ሰጥቷል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸህ ሰይድ ሙሀመድ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳን ወርን አሏህን በመፍራትና የሐይማኖቱ አስተምህሮቶችን በመተግበር ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
የእዝነትና የመተዛዘን ወር የሆነውን ረመዳን ፍፁም በዱአና በኢባዳ ፈጠሪውን በማውሳት ሊያሳልፈው ይገባልም ብለዋል፡፡
የተራቡትንና የተቸገሩት በማስፈጠር ሙስሊሙ ማህበረሰብ በረመዳን ወር ለተቸገሩ ወገኖች አጋርነቱን መግለፅ እንደሚጠበቅበት የገለፁት ኘሬዝዳንቱ የዘካ(የምጽዋት) ባህሉንም ሐይማኖቱ በሚፈቅደው መልኩ መፈፀም እንዳለባቸው አስታውሰዋል፡፡
በሃገሪቱ የተፈጠረው ሰላም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሐይማኖቱን በነፃነት መግለፅና ማስተዋወቅ እንዲቻል አድርጐታል፡፡ በመሆኑም ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተጀመረውን ልማትና ዴሞክራሲ ከመንግስት ጐን በመቆም አጋርነቱን መግለፅና ልማቱን መደገፍ ይኖርበታል ብለዋል ኘሬዝዳንቱ፡፡
መንግስት በቅርብ ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ዜጐችን ለመቀበልና ወደ ስራ ለማስገባት እያደረገ ያለውን ስራ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከጐኑ በመቆም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡
የ1 ሺህ 4 መቶ 38ተኛ የሂጅራና የሀጅ ምዝገባ መጀመሩንም የምክር ቤቱ ኘሬዝዳንት ጠቁመዋል፡፡
ጀማል ሙሐመድ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3406093
  • Unique Visitors: 192814
  • Published Nodes: 2592
  • Since: 03/23/2016 - 08:03