መውለድ ለማይችሉ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል በኢትዮጵያ ሊቋቋም ነው

ባህር ዳር፡ ግንቦት 16/2009 ዓ/ም(አብመድ)መውለድ ለማይችሉ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል (ፈርቲሊቲ ሴንተር) በኢትዮጵያ ሊቋቋም ነው፡፡

ማእከሉን የሚያቋቁመው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሲሆን፥ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ማእከሉ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የመውለድ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ሕክምና የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል።

በሆስፒታሉ የማህጸንና ጽንስ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ፌይሩዝ ሱሩር፥ ቀደም ሲል በአገሪቱ ህግ ሕክምናውን መስጠት የማይፈቀድ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ሕክምናውን የሚደግፍ የሕግ ማዕቀፍና መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የገለጹት።

ማዕከሉን በአዲስ አበባ ለማቋቋም አስፈላጊው ቦታ ተመርጦ የተዘጋጀ ሲሆን፥ የህክምና መሳሪያዎችን የሚያቀርብ፣ ለባለሙያዎች ስልጠና የሚሰጥና ሌሎች ስራዎችን የሚያከናውን የውጭ ድርጅት ቅጥር በጨረታ ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ፌይሩዝ ገለፃ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለመውለድ ችግር ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚሆኑ ጥንዶች ላይ ይከሰታል።

ያለመውለድ ችግር ስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ያለው በመሆኑ ሕክምናው አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ማዕከሉን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ማዕከሉን ለማቋቋም እየተሰሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ማዕከሉ የሚቋቋመው በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በመንግስት ድጋፍ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3870093
  • Unique Visitors: 214834
  • Published Nodes: 2859
  • Since: 03/23/2016 - 08:03