Bekur Amharic

Deatail:

የቆዳ ፋብሪካዎች ስጋት ደቅነዋል

ባሕር ዳር፡ ጥር 30 / 2009 ዓ.ም (አብመድ)በኩር ፡-  በአማራ ክልል ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ይገኛሉ:: ሁለቱ በዋና ከተማዋ ባህርዳር የተቋቋሙ ሲሆን ቀሪዎቹ በመርሳ፣ ሃይቅ፣ ኮምቦልቻና ደብረ ብርሃን ከተሞች የሚገኙ ናቸው:: የክልሉ የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ እንደሚጠቁመው ሁሉም ፋብሪካዎች ሃገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን እንዲሁም ለመስኩ የወጣውን ህግ በመተላለፍ በማህበረሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ:: ከእነዚህ ፋብሪካዎች በጠጣርና በፈሳሽ መልክ የሚወጡ በካይ ንጥረ ነገሮች ከሚፈቀደዉ በላይ ወደ አካባቢ ይለቀቃሉ:: 
መረጃዎች በተጨማሪ አንደሚያመለክቱት ከቆዳ ፋብሪካዎች ከ35 ዓይነት በላይ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ አደገኛ የሆኑ በካይ ኬሚካሎች ወደ አካባቢ ይለቀቃሉ:: እነዚህ ኬሚካሎች የልቀት መጠናቸው በህግ ከተቀመጠው ገደብ ካለፈ አደገኛ ካንሰር፣ የዘረመል ለውጥ፣ የአእምሮ ዝግመት፣ የአካል መዛባት፣ ተጣብቆ የመወለድና የባህሪ ለውጥ የሚያስከትሉ ናቸው:: አብዛዎቹን የብክለት በሽታዎች ደግሞ በህክምና ማዳን አለመቻሉ ስጋቱን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል:: በተለይ ለቆዳ ማልፊያ የሚውለው ክሮሚየምና የሜሪኩሪ ኬሚካሎች በአደገኝነታቸው የሚታወቁ ናቸው::
የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት እነዚህ የሚመክኑና የማይመክኑ የቆዳ ፋብሪካ በካይ ንጥረ ነገሮችን በጥንቃቄ ማከም ካልተቻለ የሚያስከትሉት ቀውስ ከፍተኛ ይሆናል:: ከዚህ አንፃር በአማራ ክልል የተቋቋሙት ስድስቱ ፋብሪካዎች ደካማ የኬሚካል ማከሚያ መሳሪያ (treatment plant) እና አያያዝ ያላቸው መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል:: ፋብሪካዎቹ ከሚያመነጩት በካይ ተረፈ ምርት ውስጥ ተጣርቶ ወደ አካባቢ የሚለቀቀው 35 በመቶው ብቻ ነው:: ቀሪው ብክለት ካለምንም ማጣራት ወደ አካባቢ ይለቀቃል:: አንዳንዶች ደግሞ ምንም ማጣሪያ የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል:: ለመሆኑ የእነዚህ ፋብሪካዎች አሳሳቢነት እስከምን ድረስ ነው? የነዋሪዎችን ሮሮ፣ የተፈፀሙ ስህተቶችን፣ የቁርጠኝነት ችግሩንና ዘላቂ መፍትሔውን በትንታኔያችን እንመለከታለን:: ይህንን በተግባር ለማስደገፍም በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው የጥቁር ዓባይ ቆዳ ፋብሪካን በማሳያነት ተጠቅመናል::

የነዋሪዎችና የፋብሪካው ፍጥጫ

ከሚኖሩበት የገጠር ቀበሌ ልጃቸውን ለመጠየቅ ወደ ደብረ ብርሃን የመጡት ወ/ሮ ጌጤ በላይሁን ዳግም ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም፤ ወ/ሮዋ አንገትና ደረታቸው አካባቢ ታመው አልጋ ላይ ተኝተዋል:: ጎላ ብሎ ይሰማ የነበረው አንደበታቸውም ከመዘጋት ባልተናነሰ እጅጉን ተዳክሟል::
ወ/ሮ ጌጤ በሽታቸውን ለማወቅ ሁለት ጊዜ ያህል ወደ ህክምና ተቋም ቢመላለሱም “በሽታው ከአቅም በላይ ነው!” በሚል ፈውስ አላገኙም:: ከሀገር ቤት ሲመጡ ፍፁም ጤነኛ የነበሩት ወ/ሮዋ በአንዲት ጀንበር ልሳናቸውን አጥተዋል:: እርሳቸው እንደሚሉት ከፋብሪካ በሚወጣ ብናኝና ሽታ መጠቃታቸው በህክምና ባለሙያዎች ተነግሯቸዋል:: 
እርሳቸው የሚገኙበት የልጃቸው መኖሪያ ቤት የደብረ ብርሃን ቆዳ ፋብሪካን ተጐራብቶ ይገኛል:: ከዚህ ፋብሪካ የሚወጣው ሽታ ደግሞ እጅግ ከባድ ነው:: ከዚህ ሽታ ይገላግላቸው ዘንድ ልጃቸውን ቤት ተከራይቶ እስኪወስዳቸው ድረስ ተማጽነውታል:: በተለይም ማታ ማታ ሽታው ከባድ እንደሚሆንና ቤቱ ሙሉ ለሙሉ እንደሚበከል ገልፀዋል:: በዚህ ሽታ የተጠቁት ወ/ሮ ጌጤ ከማያውቁት በሽታ ጋር መኖር ከጀመሩ ከአንድ ወር በላይ ሆኗቸዋል::
ሌላኛው ነዋሪ አቶ ትእዛዙ ከላለው ወደ አካባቢው የመጡት ቤት ገዝተው ነው:: አቶ ትእዛዙ ቤት ከመግዛታቸው በፊት በአካባቢው የዱቄት ፋብሪካ እንጅ የቆዳ ፋብሪካ ስለመኖሩ አያውቁም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ ያኔ ፋብሪካው ስራ ማቆሙ ነው:: ትእዛዙ በተዘጋው ልሳኑ፣ “አንድ ቀን ቤት ከፍቼ ስወጣ ከባድ ሽታ ከውጭ ተቀበለኝ:: ወዲያውኑ በጣም ካስነጠሰኝ በኋላ ማስመለስ ጀመርኩ:: ወደ ህክምና ሄጄ ምርመራ ሳደርግ ችግሩ በሽታ ምክንያት የመጣ እንደሆነ ባለሙያዎች ነገሩኝ:: በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ ሄጄ መታከም ካልቻልኩ ደግሞ ለጤናየ አስጊ እንደሚሆን ነገሩኝ:: አዲስ አበባ ሄጄ ምርመራ ባደርግም ጉሮሮየ ክፉኛ በመጠቃቱ ቀዶ ህክምና እንዳደርግ መከሩኝ:: ነገር ግን ተመልሸ ወደዚህ ስመጣ ተጠቂ ስለምሆን ህክምናውን አላደረግሁም:: ትክክለኛ ድምጽ ነበረኝ:: አሁን ግን ተዘግቷል:: ለመተንፈስም አቸገራለሁ:: በዚህ ሁኔታ ስኖር አንድ አመት ሞልቶኛል” ብሏል::
የጥቁር ዓባይ ቆዳ ፋብሪካ በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በ 07 ቀበሌ የሚገኝ የግል ፋብሪካ ነው:: ተቋሙ ከሶስት ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን በቀን እስከ አንድ ሺህ 500 በጨው የታጀለ የበግና የፍየል ቆዳን ወደ አለቀለት የቆዳ ምርት ይቀይራል:: ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በዚህ ፋብሪካ የብክለት ልቀት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው:: የቆዳውን ፀጉር ለማላቀቅ የሚጠቀሙበት ኬሚካልና የሚለቀቀው የፍሳሽ ቆሻሻ ምንም አይነት ማጣራት እንደማይደረግበት ይገልፃሉ:: 
አቶ አብርሃም ረጋሳ የተባሉ ነዋሪ ሽታው ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት እስከ 5፡00 ሰዓት እንዲሁም ሌሊት ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እንደሚለቀቅ ተናግረዋል:: “ሽታው በቀጥታ ቤት ውስጥ ስለሚገባ ህፃናትን በጤና ማሳደግ አልቻልንም:: ሁሌም የጉንፋን ተጠቂ ናቸው:: እኛም “የሳይነስ” በሽታ ተጐጅ ሆነናል:: ቤቱን ሸጠን እንዳንሄድ የሚገዛን አናገኝም:: ጥለነው እንዳንሄድ ደግሞ ንብረት ሆኖብን ተቸግረናል” ብለዋል::
የፋብሪካው የምርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ሽፈራው ፋብሪካው ምንም አይነት ብክለት እንደሌለው ይናገራሉ፤ “ሁለት ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የመጀመሪያ የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብተናል:: ክሮሚየም የተባለውን ኬሚካልም ከዋናው ፍሳሽ ለይተን እንዲታከም እናደርገዋለን:: ወደ አየር የሚለቀቀው ብናኝ ደግሞ አነስተኛ ነው:: በሰዎች ጤና ላይ ተፅዕኖ የለውም:: ሰዎች ስለሚፈሩ ነው ይህን ስጋት የሚናገሩት:: ፍሳሹን በመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ አክመን ወደ በሬሳ ወንዝ እንለቀዋለን:: በሰዓት እስከ አምስት ሽህ ሊትር ፍሳሽ ይገባል:: ወደ ወንዙ የሚገባውም ቢሆን ምንም ተጽዕኖ የለውም:: የማይመክኑ ደረቅ ቆሻሻዎችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እናቃጥል ነበር:: ሰዎች ተበከልን የሚሉትም በዚሁ ምክንያት ነው:: አሁን ግን አቁመናል” ይላሉ:: ፋብሪካው መንግስት ያስቀመጠውን ደረጃና ህግ አክብሮ እንደሚሰራም እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል::
በ2008 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት የተደረገ የመስክ ቁጥጥር ዘገባ ግን የፋብሪካውን ሥራ አስኪያጅ አባባል ሙሉ ለሙሉ የሚሽር ነው:: ዘገባው እንደሚያሳየው ፋብሪካው የፍሳሽ፣ የደረቅ ቆሻሻና የአየር በካይ ንጥረ ነገሮች አወጋገድ እጅግ ደካማ መሆኑን ነው:: ከዚህ በተጨማሪም የሚጠቀመው የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ከደረጃው በታች መሆኑን አረጋግጧል:: 
ሚኒስቴሩ ባደረገው የናሙና ምርመራ ውጤት የፋብሪካው የልቀት ደረጃ ለዘርፉ ከተፈቀደው ውስን ጣሪያ ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ሥጋት የደቀነ ነው:: ለማሳያነት ሰስፔንድድ ሶሊድ የሚፈቀደው 50 ሚሊ ግራም በሊትር ሲሆን በፋብሪካው አንድ ሺህ ሃምሳ ሚሊ ግራም በሊትር ሆኖ ተገኝቷል:: ክሎራይድ የሚፈቀደው አንድ ሺህ ሚሊ ግራም በሊትር ሲሆን ፋብሪካው ከስምንት ሺህ 543 በላይ ሚሊ ግራም በሊትር ተጠቅሟል:: የቤተ ሙከራ ውጤቱ እንደሚያሳየው ፋብሪካው ከተፈቀደው የልቀት ደረጃ ጣሪያ በላይ መሆኑን ነው :: 
ይህ ደግሞ በአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ (300/1995) ላይ “ማንም ሰው ተገቢውን የአካባቢ ደረጃ በመተላለፍ አካባቢን ሊበክል ወይም በሌላ በኩል እንዲበክል ሊያደርግ እንደማይፈቀድለት” የሚለውን ህግ ይተላለፋል፤ ከዚህ በተጨማሪም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የኢንዱስትሪ ብክለት መከላከያ (ደንብ ቁጥር 159/2002) “ፋብሪካው በካይ ነገር እንዳያመነጭ የማድረግ፣ የማይቻል ከሆነም ከተፈቀደው ጣሪያ ሳያልፍ አካባቢያዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያስወግድ” ሲል የተጣለበትን ግዴታ ጥሶ መገኘቱን ገልጿል:: በአጠቃላይ ፋብሪው የሚያመነጨው በካይ ኬሚካል ከመኖሪያ አካባቢ ቅርበት አንፃር ሲታይ የከፋ ያደርገዋል:: 
ለመሆኑ በመኖሪያ ቤቶችና በፋብሪካው መካከል እንዲህ አይነት ቅርርብ ለምን ተፈጠረ
በአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ፈቃድ ምርመራና ቁጥጥር የሥራ ሂደት መሪ አቶ አበባው አባይነህ እንደሚያብራሩት አንድ የቆዳ ፋብሪካ ከመኖሪያና ከማህበራዊ ተቋማት ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ መራቅ ይኖርበታል:: ፋብሪካዎች ርቀው ቢተከሉም ልቃታቸው ከነዋሪዎች ጋር የሚገናኝ ከሆነ ችግሩ የከፋ ይሆናል ይላሉ:: ከዚህ አንፃር የደብረ ብርሃን ቆዳ ፋብሪካን ለነዋሪዎች በእጅጉ የቀረበ ሆኖ እናገኘዋለን፣ የፋብሪካው ፍሳሽ ደግሞ በግምት ሁለት ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው በሬሳ ወንዝ ጋር በቀጥታ ይቀላቀላል:: 
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ (ኢንቨይሮመንታሊስት) የሆኑትና በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን በማማከር ላይ የሚገኙት አቶ ነጋሽ ታምሩ ፋብሪካው ካለው የመጀመሪያ የማጣሪያ ደረጃ አንፃር ወደ ወንዙ የሚደረገው ልቀት አደገኛ የሚባል ነው ይላሉ:: “በደንብ እንዲጣራ ከተፈለገ ሁለተኛ ማጣሪያ ያስፈልገዋል:: ፋብሪካው ያንን አላደረገም:: ስለዚህ በወንዙ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች፣ እንስሳትና እፅዋት የዚህ ተጠቂ ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ላቦራቶሪና ሙያተኛ የለውም:: የሚለቀውን የብክለት ደረጃ እንኳ አያውቅም:: ይህንን እንዲያስተካክሉ መክረናቸዋል” ብለዋል::
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት ፋብሪካው አሁን በቆመበት አካባቢ ምንም አይነት መኖሪያ ቤቶችም ይሁን ተቋማት አልነበሩም:: አሁን ግን ከሶስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች፣ ትምህርት ቤትና የዱቄት ፋብሪካ ከፋብሪካው እጅግ በቀረበ ሁኔታ ይገኛሉ:: ለመሆኑ እንዲህ አይነቱ የአሰፋፈር ስህተት እንዴት ተፈፀመ?
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ታገል አምሳሉ “…የጋራ ጥፋት ነው:: አንድ ፋብሪካ ቦታ ሲወስድ ከአካባቢ ተጽዕኖ ነፃ ሆኖ ሊሰራ ነው:: በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ ለፋብሪካው ራቅ ያለ ቦታ አለመስጠቱና በቅርበት ከሰጠ በኋላም የቤት ማህበራትን በዙሪያው ማስፈሩ ተገቢ አልነበረም:: ይህ በወቅቱ የተፈፀመ የአቅም ክፍተት ነው” ሲሉ ገልፀዋል::
እንዲህ አይነቱ ችግር በደብረ ብርሃን ቆዳ ፋበሪካ ላይ ብቻ ያለ አይደለም:: ከዚህ በፊት የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ተዘዋውሮ የተመለከታቸው የባህርዳር፣ የመርሳና የሃይቅ ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙ ናቸው:: አብዛኞቹ የቆዳ ፋብሪካዎች ክልሉ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ስርዓትን ከመዘርጋቱ በፊት የተቋቋሙ በመሆናቸው እስካሁን ድረስ ከሁለት ፋብሪካዎች በስተቀር የተጽዕኖ ግምገማ ሰንድ ማቅረብ አልቻሉም::

ከፈረሱ ጋሪው

የቆዳ ፋብሪዎች የሃገር ውስጥን የኢንዱስትሪ ቆዳ ፍላጐት ከማሟላት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክ ትልቅ የኢኮኖሚ አውታር ናቸው:: ነገር ግን ይህ የኢኮኖሚ ጥቅም ፋብሪካዎችን አይነኬ ተቋማት አስመስሏቸዋል:: አብዛኞቹ የቆዳ ፋብሪካዎች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ የከፋ ሆኖ እያለ ለምንዛሬ ሲባል ቸል የተባሉ ይመስላል:: 
የአካባቢ ፈቃድ ምርመራና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ አበባው በዚህ ይስማማሉ፤ “መንግስት ለኢኮኖሚ ጥቅሙ እንጅ ለአካባቢ ጥበቃ ያን ያህል ትኩረት ሰጥቷል ብየ አላምንም”ይላሉ:: ይህንን ሀሳብ በተግባር የሚያረጋግጡት ደግሞ ከንቲባ ታገል አምሳሉ ናቸው:: በደብረብርሃን ቆዳ ፋብሪካ ላይ ለምን እርምጃ አልተወሰደም ተብለው ሲጠየቁ “በአንድ በኩል ለሃገርና ለህዝብ እየሰጠ ያለው ጠቀሜታ አለ:: ፋብሪካው የውጭ ምንዛሬ ያመጣል:: ለአካባቢው ዜጐችም የስራ እድል ፈጥሯል” በማለት ፋብሪካው የሚያመነጨውን ብክለት ከሚያመነጨው ገቢ ጋር ያወዳድራሉ:: 
አቶ አበባው ግን ይህ “ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም እንደማለት ነው” የሚል ሃሳብ አላቸው “የቱንም ያህል የኢኮኖሚ አቅም ቢገነባ አካባቢን መጠበቅ ካልቻልን ኪሳራው እጥፍ ነው:: አካባቢን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል:: ለዚህ መፍትሔው ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን አጣምሮ መሄድ ነው፤ አንደኛው የኢኮኖሚ አዋጭነት፣ ሁለተኛው የማህበረሰብ ጤናማነትና ሶስተኛው የአካባቢን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ በጋራ አጣምሮ መስራት ያስፈልጋል” ሲሉ ገልፀዋል::

የቁርጠኝነት ማነስ
የቆዳ ፋብሪካዎች የብክለት ሥጋት እንዲጨምር ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ የቁርጠኝነ ማነስ ነው:: በክልሉ ያሉ የቆዳ ፋብሪካዎች ምንም እንኳ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ከአካባቢ ብክለት አንፃር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል:: ሁሉም የቆዳ ፋብሪካዎች ደረጃቸው ዝቅተኛ፣ የብክለት መጠናቸው ደግሞ ከፍተኛ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል:: ነገር ግን ይህ መሆኑ እየታወቀ በፋብሪካዎቹ ላይ የእርምት እርምጃ ሲወሰድ አይታይም:: የክልሉን መንግስት አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ በተግባር እናስደግፈው ከተባለ የመጀመሪያው የወጡ ህግና ደንቦችን አለማስፈፀሙ ነው:: በኢትዮጵያና በክልሎች የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርን በሚመለከት በቂ ሊባሉ የሚችሉ ህጐች ወጥተዋል:: (የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1995፣ የኢንዱስትሪ ብክለትን ለመከላከል የወጣ ደንብ 159/2001፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ቁጥር 513/1999፣ የአ.ብ.ክ.መ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 181/2003) ማየት በቂ ነው:: 
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ጉዳትና ስጋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጅቶችን እስከ መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር ለክልሎች ስልጣን ሰጥቷል:: 
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነሃሴ 25/2008 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ የኦሮሚያ ክልል ይህንን ህግ ተጠቅሞ አካባቢን በክለዋል ባላቸው ስድስት ፋብሪካዎች ላይ እገዳ ጥሏል:: እነዚህ ፋብሪካዎች “በውሃ አጠቃቀምና በፍሳሽ አወጋገድ ስርዓታቸው ብክለት አስከትለዋል” በሚል የተዘጉ ናቸው:: 
በአንፃሩ በአማራ ክልል በህብረተሰብ ጤና ላይ ትልቅ አደጋ የደቀኑት እነዚሁ ፋብሪካዎች አሁንም ድረስ ህግ እየጣሱ ስራቸውን ቀጥለዋል:: ለማሳያነት እንኳ ከፍተኛ ብክለት እንደሚለቅ በምርመራ የተረጋገጠበት የደብረ ብርሃን ቆዳ ፋብሪካ አስቸኳይ እርምት እንዲወስድ ቢጠየቅም ከሁለት ሳምንት በፊት ለክልሉ አካባቢ፣ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ ምንም ለውጥ አለማድረጉ ተገልጿል:: ይህንን ቁርጠኝነት የማጣት ድክመት የክልሉን ተቋም ጥርስ የሌለው አንበሳ አድርጐታል ሲሉ አቶ አበባው ይገልፁታል::
“ብዙ የአካባቢ የህግ ማእቀፍ ወጥተዋል:: ነገር ግን እየተተገበሩ አይደለም:: ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው:: እስካሁን መውሰድ የሚገባንን እምርጃ መውሰድ አልቻልንም:: በእኛ ላይ ሳይቀር ጫና ይደርስብናል:: እኛ እርምጃ እንውሰድ ስንል ልክ እንደ ልማት አደናቃፊ ነው የምንታየው:: በአጠቃላይ የተሰጠንን ስልጣን መጠቀም አልቻልንም” ሲሉ ገልፀዋል::

ምን እንጠብቅ?
በቆዳ ፋብሪካዎች ዙሪያ የሚኖሩት እነ አቶ ትዛዙም ሆኑ ሌሎች ነዋሪዎች የአካባቢ ብክለቱ አንዳች መፍትሔ እንዲያገኝ ይሻሉ:: መፍትሔ ፍለጋም በተደጋጋሚ የመንግስት ተቋማትን በሮች አንኳኩተዋል:: የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ ታገለ አምሳሉ በበኩላቸው “ከዚህ በኋላ ፋብሪካው ከብክለት የፀዳ አሠራርን የሚከተል ከሆነ ያንን መተግበር፣ አለበለዚያ ከክልሉ መንግስት ጋር ተባብሮ ፋብሪካውን ነቅሎ በኢንዱስትሪ መንደሩ እንዲተከል ማድረግ የሚል የግል ሐሳብ አለኝ” ይላሉ::
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው (ኢንቨይሮመንታሊስቱ) ነጋሽ ታምሩ ግን በዚህ አይስማሙም:: ፋብሪካውን መንቀል ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ከመሆኑ አንፃር ከመንቀል ይልቅ የማጣራት ሂደቱን ይበልጥ ዘመናዊ ማድረግ፣ ተረፈ ምርቱን ከማቃጠል ለስራ እድል መፍጠሪያ መጠቀምና ቆሻሻዎችን እንደገና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም በጋራ ተባብሮ መስራትን ይመክራሉ::
የአካባቢ ፈቃድ ምርመራና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ አበባየሁ በበኩላቸው “የፖለቲካ አመራሩ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠትና በቁርጠኝነት መስራት፣ ተጽዕኖዎችን መጋፈጥና ጉዳት ያስከተሉ ፋብሪካዎችን በህጉ መሠረት እስከ መዝጋት መሄድ ይገባል” የሚሉ ሃሳቦችን በመፍትሔነት አስቀምጠዋል::
ዶ/ር በላይነህ አየለ የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው:: እርሳቸውም “በእርግጥ ለአካባቢ ጥበቃ ከሰጠነው ትኩረት ይልቅ ለኢንዱስትሪ የተሰጠው ትኩረት ይበልጣል:: ሁሉም የክልሉ የቆዳ ፋብሪካዎች ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ያሉበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው:: 
“እነዚህ ፋብሪካዎች በተቀመጠላቸው ደረጃ ካልሰሩ ቁጥጥር አድርጐ መክሰስ ተገቢ ነው:: ይህንን እስካሁን አልሞከርነውም:: በቅርቡ የህግ ባለሙያ መደብ ሲፈቀድልን እንተገብረዋልን:: በእርግጥ የደብረ ብርሃንን በሚመለከት በቂ መረጃ ኣልነበኝም:: አሁን ከነገርከኝ ጀምሮ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እልካለሁ:: በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማስተካከያ ካላደረጉ ወደ ክስ እናመራለን:: ከዚህ በኋላ ትልቅ ትኩረት ሰጥቼ የምሰራበት ዘርፍ እንደሚሆን ቃል እገባልሃለሁ” ብለዋል::

February 7, 2017

Pages

Visitors

  • Total Visitors: 3161786
  • Unique Visitors: 186711
  • Published Nodes: 2579
  • Since: 03/23/2016 - 08:03