Bekur Amharic

Deatail:

“የጣና ዓሣ ደህንነት ቋፍ ላይ ነው”

ባህር ዳር፡ ሀምሌ 10 /2009 ዓ/ም (አብመድ)አቶ ይበልጣል ዓይናለም በአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ማስፋፊያ ኤጄንስ የዓሳ ሀብት ልማትና አስተዳደር ባለሙያ ናቸው:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ርባታና ጤና (አኒማል ፕሮዳክሽን ኤንድ ኼልዝ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዓሳ ሀብትና እርጥበት አዘል መሬት አስተዳደር (ፊሸሪ ኤንድ ዌትላንድ ማኔጅመንት) ተከታትለዋል:: በሙያቸው በወረዳ፣ ዞንና ክልል በእንስሳት መኖ እና በዓሣ ሀብት ዙሪያ አገልግለዋል፤ አሁንም በሥራ ላይ ናቸው:: አቶ ይበልጣልን የዚህ ዕትም የበኩር እንግዳችን አድርገን ስለዓሳ ሀብታችን አጠቃላይ ጉዳዮችን ተጨዋውተናል፤ መልካም ንባብ!

እንደ ክልል የዓሣ ሀብት አቅማችን ምን ያህል ነው?

ለዓሣ ሀብት መሠረቱ ውኃ ነው፤ ክልላችን ከዚህ አኳያ በጣም ሀብታም ነው:: በኢትዮጵያ ትልቁን ሐይቅ ጣናን ጨምሮ በርካታ ሐይቆችና ትልልቅ ወንዞች፣ ሰው ሠራሽ ግድቦች በክልሉ አሉ:: ከሀገሪቱ የውኃማ አካል ሽፋን 36 ከመቶውን የሚይዘው ጣና ሐይቅ ነው፤ የዚህ ሁሉ ውኃማ አካል ባለቤት መሆናችን በዓሣ ሀብትም ትልቅ አቅም እንዲኖረን አድርጓል:: በዚህ አቅማችን ልክ ወደ ዓሣ ግብርና ብንገባ ከክልሉ አልፎ ሀገሪቱን መመገብ የሚያስችል አቅም አለ::

ዓሣን የመመገብ ልምዳችንስ?

በአመጋገብ ዙሪያ ቀደም ሲል የነበረን ልምድ ከዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: በርካታ የጽሑፍ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዓሣን በመመገብ በክልላችን የነገደ ወይጦ ማኅበረሰብ አባላት ቀዳሚዎች ነበሩ:: ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ግን ዓሣን መመገብ አያዘወትርም ነበር:: በአሁኑ ወቅት ግን በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ የመመገብ ልምዱ አለ፤ የመመገብ ልምዱ የማደጉን ያህል የዓሣ ምርታችን ባለማደጉ ግን አቅርቦቱ ተመጣጣኝ መሆን አልቻለም:: በተለይ ከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የዓሣ ተመጋቢ አለ:: ወደ አርሶ አደሩም አካባቢ ዓሣ የመመገብ ከፍተኛ ፍላጎት አለ፤ የሚጎድለው የአመጋገብ ብልሀቱን ማወቅ ነው:: በዚህ ዙሪያም ግንዛቤ የመፍጠር ጅማሮዎች አሉ:: በተለይ እንደ ተከዜ ተፋሰስ ባሉት አዲስ የዓሣ አቅርቦት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የአመጋገብ ስልጠና በስፋት መስጠት ያስፈልጋል::

ዓሣን መመገብ የሚያስገኘው የተለዬ ጠቀሜታ አለ?

አዎ! ዓሣ በባሕሪው እንደ ወተት የተመጣጠነ ንጥረ-ምግብ የያዘ ነው:: ዓሣ ለአካል ግንባታ፣ ለአጥንትና ጥርስ ጥንካሬ፣ ለኃይል ምንጭ፣ … የሚሆኑ ንጥረ ምግቦችን የያዘ ነው:: እንደ ሌሎች የምግብ ዓይነቶች አንድና ሁለት ብቻ ጥቅም የሚሰጥ አይደለም፤ ለአካልና አዕምሮ ዕድገት ጭምር በጣም ጠቃሚ የምግብ ይዘት አለው:: ብቻውን እንኳ የተመጣጠነ ምግብ ነው፤ በዓለም ላይ ምርጥ ምግብ የሚባለውም እርሱ ነው:: በሁለተኛው የዕድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ዘመን መጨረሻ እንደ ግብ በኤጀንሲያችን ያስቀመጥነውም በክልሉ የዓሣ ተመጋቢነትን በማሳደግ መቀንጨርን መከላከል ነው::

ዓሣን በየትኛው የአየር ንብረት ክልል በሚገኙ ውኃማ አካላት ነው ማርባት የሚቻለው?

በሁሉም የአየር ንብረት ክልል ማራባት ይቻላል:: "ዘመናዊ የዓሣ ግብርና" የሚባል አዲስ የዓሣ እርባታ ዘዴ መጥቷል:: በዚህ ዘዴ ማንኛውም ሰው 10 ሜትር በ10 ሜትር የሆነ ስፋት (100 ካሬ ሜትር) ያለው ገንዳ በማዘጋጀት ዓሣ ማርባት ይችላል:: በዝርያ ደረጃ የደጋ፣ የወይና ደጋና የቆላ የሚሆኑ ዓሦች አሉ:: 
እንደ ክልልም ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ እየጀማመርን ነው:: ልክ የዶሮ ጫጩት በማስፋልፈል ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ሥራ እንደሚከናወነው ሁሉ በዓሣ ዘርፉም ጫጩት እያባዙ በገንዳ ለሚያራቡ አርሶ አደሮች ለመስጠት የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ:: በግብርና ዕድገት ፕሮግራም ድጋፍ ባሕር ዳር ላይ የዓሣ ጫጩት ማረቢያ ማዕከል ለመገንባት የዲዛይን ሥራው እያለቀ ነው፤ በቅርቡ ግንባታው ይጀመራል:: 
ስለዚህ ዓሣ በየትኛውም የአየር ክልል መራባት ይችላል፤ አርሶ አደሩም በያለበት ከመስኖ ሥራው ጎን ለጎን በዓሣ እርባታም እንዲሠማራ ለማድረግ እየተጀማመረ ነው:: ትልቁ መልካም ዕድል ደግሞ የአገራችን ውኃማ አካላት እንደ ሰለጠነው ዓለም ውኃማ አካላት አልተበከሉም:: በመስኖ ግድቦች አካባቢ ሁሉ ዓሣ በሚገባ ማርባት ይቻላል:: ምናልባት በመስኖ ግድቦች አካባቢ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ውኃውን ወደ ማሳ ለማጠጣት በቱቦ ስናሳልፍ ዓሦችም አብረው እንዳይሄዱ ማጣሪያ መግጠሙ ላይ ነው:: ከመስኖው ውኃ ጋር አብረው ወደ ማሣ ከገቡ ስለሚሞቱ ማጣሪያ የግድ ያፈልጋል:: ይህ እንዲሆን ለሚገነቡ አካላት አስተያዬት እየሰጠን ነው:: ከዚህ በፊት ለምዱ ስላልነበረ ግድቦቹ ይህንን ችግር የሚፈቱ አልነበሩም:: 
በተለይ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶቻችን ደግሞ ሲጠናቀቁ ለዓሣ ግብርናችን ማደግ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ተስፋ ተጥሎባቸዋል:: በሕዳሴ ግድቡ አማካኝነት በሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች በዓሣ ግብርና የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል:: ለዚያም አካባቢ የሚሆኑ የሞቃታማ የአየር ንብረት ክልል የዓሣ ዝርያዎች ስላሉን::

ጣና ሐይቅ በዓሣ ዝርያ ሀብታም ነው?

በጣም እንጅ! በርካታ ባለሙያዎች በጣና ሐይቅ የዓሣ ዝርያ ዙሪያ ጥናቶችን አካሂደዋል:: ከሀገራችን ዶክተር እሸቴ ደጀኔና ዶክተር አያሌው እንዲሁም በርካታ የውጭ ዜጎች የጻፏቸው ጥናቶች አሉ:: እነዚያ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በሐይቁ ቀረሶ፣ ቤዞ፣ አምባዛና ነጭ ዓሣ የሚባሉ አራት ዋና ዋና ዝርያዎች አሉ:: የነጭ ዓሣ ዝርያዎች ደግሞ በሥራቸው ወደ 27 እንደሚደርሱ ጥናቶቹ ያሳያሉ:: እነዚህ ዝርያዎች በራሳቸው በሌሎች ሀገራት ውኃማ አካላት የማይገኙ ብርቅየዎች ናቸው:: ሌሎቹም ዝርያዎች በሥራቸው በርካታ ንዑሳን ዝርያዎች አሏቸው:: ስለዚህ በዝርያ ይዘቱ ጣና የዓሣ ባለሀብት ነው::

የጣና የዓሣ ሀብት ስጋት ውስጥ መሆኑን የሚናገሩ ሰዎች አሉ፤ እውነት ስጋት ውስጥ ነው?

በሚገባ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው፤ የዓሳ ሀብቱ ብቻ ሳይሆን ሐይቁም ስጋት ተጋርጦበታል:: አንደኛው የስጋት ምንጭ ህገ-ወጥ መረብ ነው:: ሕገ-ወጥ መረቡ አይመርጤ በመሆኑ ከትልቅ እስከ ትንሽ ዓሦችን ሳይመርጥ የሚይይዝ ነው:: ከትንሽ እስከ ትልቅ በሁሉም ዕድሜ ክልል ያሉ ዓሦች ከተያዙ ደግሞ ዘር ሳይተኩ ይሞታሉ ማለት ነው:: ይህ አይመርጤ መረብ ከግብፅ አሌክሳንደሪያ በሱዳን በኩል አድርጎ በሕገ-ወጥ የሚገባ ነው:: 
ሕገ-ወጥ አስጋሪም ሌላኛው የሥጋት ምንጭ ነው:: በቅርቡ የመጣው እምቦጭ አረም ደግሞ ከሁሉም የከፋው ስጋት ሳይሆን አይቀርም:: ከሆቴሎችና ሌሎች ተቋማት ወደ ሐይቁ የሚለቀቁ በካይ ኬሚካሎችም በስጋትነት ይነሳሉ:: እነዚህን ስጋቶች ለመቅረፍ በጋራ እስካልተሠራ ድረስ የዓሣ ሀብታችን በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው:: አሁን ላይ የጣናና የዓሦች ደህንነት በቋፍ ላይ ነው:: የሁሉንም የኅበረተሰብ ክፍልና የመንግሥት አካላት የተቀናጀ እገዛ ይፈልጋሉ:: 
በነገራችን ላይ ጣና ሐይቅን መታደግ ያለብን ለዓሣ ሀብታችን ብለን ብቻም አይደለም:: በጣና ዙሪያ የሐይቁን ባሕር ሸሽ እና ውኃውን በሞተር ስበው የሚተዳደሩ ሚሊዮን አርሶ አደሮች አሉ፤ የጀልባ ባለቤቶችና ዓሣ አስጋሪዎችም በሥራቸው በ10 ሺህ የሚቆጠር ቤተሰብ ሊኖራቸው ይችላል::
ከዚህ ባለፈ ጣናን የሕልውናቸው መሠረት ባደረጉት ደሴቶች የሚኖሩ ገዳማትና መነኮሳት አሉ:: እነዚህ ሁሉ ሕይወቶች የሚቀጥሉት ጣና ደኅንነቱ ሲጠበቅ ነው:: ስለዚህ የእንስሳት ሀብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ፣ የክልሉ የፀጥታ አካል፣ የዙሪያው አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ በሐይቁ ዙሪያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች፣ … ሁሉ ተቀናጅተው ጣናን የመታደግ ሥራ መሥራት አለባቸው::

ሕገ-ወጥ መረብን መቆጣጠር ያለበት ማን ነው?

መረቡንና ተያያዥ ከዓሣ ማስገር ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሕግ ማዕቀፍ አለ:: መሠረታዊው ችግር ሕጉን የሚያስከብር አካል አለመኖሩ ነው:: በተለይ የፍትሕ አካላት ጉዳዩን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት አነስተኛ ነው:: በእርግጥ አልፎ አልፎ መረቡን በፍተሻ የመያዝ፣ የመቀማትና የማቃጠል ሥራዎች ይሠራሉ፤ ነገር ግን ማስቆም አልተቻለም:: 
ሕገ-ወጥ አስጋሪዎቹ ሕገ-ወጥ መረቡን በጉልበት ጭምር እየተጠቀሙ ነው:: መረቡን በብዛት የሚጠቀሙበት በሌሊት ሲሆን የጦር መሣሪያ ይዞ የሚቆጣጠሩትን አካላት በማስፈራራት ጭምር ሁሉ ነው:: ስለሆነም የሁሉም አካላት ቅንጅት በዚህም በኩል ያስፈልጋል:: እንደ መፍትሔ የዓሣ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ከቀበሌ እስከ ወረዳ ደረጃ በዋና አስተዳዳሪዎች የሚመራ አቋቁመናል:: የግንዛቤ ፈጠራም ሠርተናል፤ ግን መቀነስ እንጅ ማጥፋት አልተቻለም:: በነገራችን ላይ ሕገ-ወጥ መረቡን ሕጋዊ ዓሣ አስጋሪዎችም ይጠቀሙበታል፤ በድብቅ:: ስለዚህ የተቀናጀ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል::

የመራቢያ አካባቢያቸው መወረር ለዓሦች መመናመን እንደ ምክንያት ይነሳል፤ ይስማማሉ?

አዎ! የነጭ ዓሣ ዝርያዎቹ ሐይቁ ውስጥ አይራቡም፤ ለእርባታ ወራጅ የወንዝ ውኃን ይፈልጋሉ:: በዚህ የተነሳ በመራቢያ ወቅታቸው ወደ ሐይቁ ገባር ወንዞች መዳረሻ ይሄዳሉ:: በዚህ ጊዜ ወንዞች አካባቢ ለእርባታ በሄዱበት በአጥማጆች ሊያዙ ይችላሉ:: አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወንዞቹ ወደ ማሳ ይጠለፉና እንቁላሎቹም ሆኑ ዓሦቹ ይሞታሉ:: ከዚህ በመነሳት ነው በተለይ ክረምት ወቅት በጣና ሐይቅ ገባር ወንዞች መዳረሻ አካባቢ ዓሣ ማስገር የምንከለክለው::

በተለይ ከዓሣ ሀብት ጋር በተያያዘ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን ያሳያል?

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በጣም ያደገ ነው:: በአካል ሄጄ የጎበኘሁት የቻይና ልምድ እጅግ የሚያስገርም ነው:: ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ቻይና በቀን ሁለት ጊዜ ዜጎቿን ዓሣ ትመግባለች:: የዓሣ ግብርናቸው በጣም ያደገ ነው:: በአግባቡ የተቀረፀ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ፖሊሲውን በአግባቡ የሚጠቀም ሕዝብም ፈጥረዋል:: ለዓሣ ፍላጎታቸው የወንዞችና ሐይቆች ጥገኞች አይደሉም፤ በሰው ሠራሽ ኩሬዎች በየገበሬው ጓሮ በብዛት ዓሣ ይመረታል::
ካለን የውኃ ሀብትና የሕዝብ ቁጥር አንጻር ዘርፉን ብናዘምነው በአግባቡ የምግብ ዋስትናችንን የምናረጋግጥበት ነው:: የሥርዓተ ምግብ ዝንፈት ችግራችንን በመቅረፍ መቀንጨርን ሁሉ የምናስቀርበት ሀብት አለን:: እኛ ጣና ላይ በዓሣ እርባታ ምንም የሠራነው የለም፤ ቻይናውያን ግን ታሁ የሚባል ሐይቃቸውን ከፋፍለው ለባለሀብቶች በመስጠት ዓሣን በዘመናዊ መንገድ እንዲያረቡበት አድርገዋል:: ዶሮ፣ በግ ወይም ከብት እንደምናረባው በዓሣ እርባታ ቻይናውያኑ በብዛት ተሠማርተውበት የሥራ ዕድል መፍጠሪያም፣ የምግብ ዋስትናቸው ማረጋገጫም አድርገውታል:: ቻይናውያን በዘመናዊ ግብርናቸው እስከ 70 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዓሣ ለገበያ ያቀርባሉ፤ እኛ ግን ሁለትና ሦስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ዓሣም የለንም፤ ዓሣችን ግን ተመሣሣይ ዝርያ ነው::
በእርግጥ አሁን ከኛም የመጀመር አዝማሚያና ጅማሮ አለ፤ ሜጫ አካባቢ በዚህ የተሠማሩ አሉ:: ከአፍሪካም ግብፅ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ … በዓሣ ሀብት የላቀ ልምድ አላቸው:: እኛም እነዚህን ሀገራት መከተል ያለብን ይመስለኛል::

የዓሦች የመራቢያ ወቅት የተወሰነ ነው?

እንደየዝርያዎቹና የአየር ንብረት ሁኔታው የሚለያይ ነው:: ዓሣ የሚመቼው የእርባታ መጠነ ሙቀት አለ፤ ከ16 እስከ 32 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ:: በዚህ ክልል ውስጥ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ሲታከሉበት ይራባል:: ለምሳሌ ቀረሶ ዓሣ መጋቢትና ሚያዝያ ወር መራባት ይመቸዋል:: የዚሁ ዝርያ ሆነው መስከረምና ጥቅምት የሚራቡም አሉ፤ ወሳኙ ነገር ተስማሚ መጠነ ሙቀትና በቂ ምግብ ማግኘት ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞ ዓሦችን በዘመናዊ ግብርና ለማርባት ምቹ ያደርጋቸዋል::

ከጣና ሐይቅ የዓሣ ዝርያዎች የከፋ አደጋ ውስጥ ያሉት የትኞቹ ናቸው?

ብዙዎቹ ዝርያዎች ቁጥራቸው ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው ችግሮች ምክንያት እየቀነሰ ነው:: ቤዞን የሚባለው ዝርያ በተለይ በጣም በአስጊ ሁኔታ እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ:: በእርግጥ ቀጣይ ጥናቶችም ይጠይቃል፤ ግን ደግሞ ቀድም ያነሳናቸው ሥጋቶች እስካልተወገዱ ድረስ ሁሉም ዝርያዎች ችግር ውስጥ እንዳሉ መገመት አይከብድም::

ጣና ከአቅሙ በላይ አስጋሪዎችን ተሸክሟል ወይስ ከአቅሙ በታች ነው?

የጣና አቅም የተጠና ነው፤ በዓመት እስከ 15 ሺህ ቶን ዓሣ እንደሚመረት ጥናቶች ያሳያሉ:: ነገር ግን በሐይቁ አቅም ልክ በተጠና አካሄድ እየተሠራ አይደለም:: አሁን ላይ በርካቶች በጣና ላይ ዓሣ እንደሚያሰግሩ ከመግለፅ ያለፈ ቁጥራቸውን ማወቅ አይቻል ይሆናል፤ በእርግጥ በሕጋዊ መንገድ ዓሣ ለማስገር ፈቃድ ያወጡ ይታወቃሉ:: ግን እነሱ ብቻ ለማስገራቸው በእርግጠኝነት መግለፅ አይቻልም:: ዓሦቹን እየተንከባከቡ የሚያሠግሩም የሉም:: ስለዚህ አቅሙና እውነታው ላይመጣጠኑ ይችላሉ::

የጣና ባለቤት ማን ነው?

በባለቤትነት ደረጃ ሕዝቡና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው:: ሐይቁንም ለመጠበቅ የአካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና ቢሮ፣ በዙሪያው ያሉ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች፣ በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ … ሁሉ ይመለከታቸዋል:: ነገር ግን እነዚህን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚያስተባብር የራሱ የመንግሥት አካል ደግሞ ያስፈልገው ይመስለኛል:: አሁን በጥቅሉ የሁላችን ኃላፊነት ስለሆነ የተቀናጀ ሥራ መሥራት የተቻለ አይመስለኝም:: ለምሳሌ እምቦጭን ለማጥፋት አንድ ተቋም ወይም የሆነ የመንግሥት አካል በተናጠል የሚችል አይመስለኝም፤ ሁሉንም ማቀናጀት ያስፈልጋል::

ለነበረን ቆይታ አመሠግናለሁ::

እኔም አመሠግናለሁ::
በኩር ጋዜጣ ሀምሌ 11/2009 ዓ/ም ዕትም(አብርሃም በዕዉቀት)

July 17, 2017
Deatail:

 

ባህር ዳር፡ ሰኔ 13 /2009 ዓ/ም (አብመድ)“ከስህተቱ የማይማር ፈንጅ አምካኝ ብቻ ነው” የሚል ጥቅስ ከዓመታት በፊት ታክሲ ውስጥ ማንበቤን አስታውሳለሁ:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ጥቅሱን በደንብ አብላላሁት:: ከዚያም፣ “ፈንጅ አምካኝ ለምን ከስህተቱ አይማርም?” ብዬ ራሴን ጠየኩ:: በኋላ ራሴ ለራሴ መልስ ሰጭ ሆንኩና፣ “ፈንጅ አምካኝ ስህተት ከሠራ ስህተቱ ሕይወቱን ስለሚያጠፋው ከስህተቱ የሚማርበት ዕድል የለውም፤ አባባሉ የሚያስረዳው ይሄንን እውነታ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ::

አሁን ደግሞ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት የሚባል ከስህተቱ የማይማር፣ ነገር ግን ስህተቱ ያላጠፋው፤ በተደጋጋሚ በሚሠራው ስህተት ትውልድን የሚያጠፋ ተቋም እያዬን ነው:: ይሄ ተቋም ባለፈው ዓመት በፈፀመው ስህተት የፈተና ወረቀቶች ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች እጅ ገብተው በማኅበራዊ ድረ ገፆች በመለቀቃቸው የፈተናው ጊዜ ተራዘመ፤ የተማሪዎች ስነ-ልቦና ክፉኛ ተጎዳ፤ ተማሪዎቹ በራስ መተማመን እንደራቃቸው ማኅበራዊ ድረ ገፆች ተዘግተውና በይድረስ ይድረስ ፈተና ተዘጋጅቶ ተፈተኑ፤ (ትምህርት ሚኒስቴር “በመጠባበቂያነት የተዘጋጀውን ፈተና ነው ያቀረብኩት” ብሎ የነበረ ቢሆንም::

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለፈተና የተቀመጡ የአማራ ክልል የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት አስመዘገቡ:: ለፈተና ከተቀመጡት ውስጥ የማለፊያ ነጥብ ያላገኙት (የወደቁት ለማለት ያልደፈርኩት ተፈታኞች የወደቁት በእነሱ ስህተት መሆኑን ስላላመንኩበት ነው) 67 ነጥብ 51 ከመቶ ሆኑ:: ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተማሪዎችን በማሳለፍ ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ተርታ ተሰለፈ::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ “ጥናት አካሄድኩ” ብሎ ያወጣው የውጤት ትንተና የሚያሳዬው ምክንያቶቹ፡- “የተማሪዎች የመማር ፍላጎት መቀነስ፣ መምህራን ለተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጋቸው፣ የወላጆች ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆን፣ በቂ የትምህርት ግብዓት አለመሟላት፣ የፈተና አፈታተን ችግር (ሌላ ቦታ ፈተና በመሰረቁ ወይም የተሳሳተ መልስ  በመሠራቱ)፣ የማለፊያ ነጥቡ ከፍ ማለቱ፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜ መባከንና የትምህርት ይዘት አለመሸፈን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መኖር” እንደሆኑ ነው::

እንደኔ ትዝብት ግን ለችግሩ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት፣ “የአፈታተን ችግር (ሌላ ቦታ ፈተና በመሰረቁ ወይም የተሳሳተ መልስ በመሠራቱ)” የሚለው ነው:: ከዚያ ውጭ ያሉት የትምህርት ቢሮው የፈጠራቸው ሰበቦች የፈተና አዘጋጁንና የአስተዳዳሪውን አካል ለመሸፈን የቀረቡ የሚመስሉ የማያሳምኑ ሰንካላ ምክንያቶች ናቸው:: ይህ ግን “ችግሮቹ የሉም” ማለት አይደለም:: እንዲያውም የተጠቀሱት  በአብዛኛው በፊት ጎልተው ይስተዋሉ የነበሩ፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው:: የመምህራን ለተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረግ በየዓመቱ የሚነሳ ችግር እንደሆነ እናውቃለን:: ያንን ችግር ለማቃለል ብሎም ለመፍታት መንግሥት በየጊዜው መምህራንን ለማበረታት የሚወስደውን እርምጃም እናውቃለን፤ የመምህራንን መታተርም ከአንደበታቸው እንሰማለን:: ታዲያ እንዴት 32 በመቶ ብቻ ተማሪ ለማሳለፍ ይህ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል?

እንዲያው ምንም መቀባባት ሳያስፈልገው ባለፈው ዓመት ያ ሁሉ ተማሪ የወደቀው የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጉና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ፈተናው ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች እጅ በመግባቱና በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በመለቀቁ የተማሪዎች ስነ-ልቦና በመጎዳቱ የተነሳ ነው:: ሌሎቹ ምክንያቶች ምክንያት ቢሆኑም የዚህን ያክል የውጤት ማሽቆልቆል አያስከትሉም ነበር፤ ምክንያቱም በየዓመቱ የነበሩና እየተቃለሉ የመጡ ችግሮች ናቸውና::

የሚገርመው ነገር ያንን ያህል የስነ-ልቦና ቀውስ በተማሪዎች ላይ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑ ስህተት ፈጻሚዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መቀጣት አለመቀጣታቸው ወይም የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው ስለመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አለመገለፁ ነው:: ወላጅ ስንት ለፍቶ፣ “የነገ ተስፋ ይሆኑኛል፤ ሕይወቴን ይለውጡልኛል፤ እነሱም የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ” ብሎ ያስተማራቸው  ልጆቹ ውጤት እንዲበላሽ ምክንያት የሆኑ ሰዎች በጥፋታቸው ሕግ ፊት ቀርበው ሲቀጡ ሕዝቡ ማየትም ሆነ መስማት ይፈልግ ነበር:: ተማሪዎች ስንት ደክመው ተምረው፣ ዓመቱን ሙሉ ቀን ከሌሊት ድፍት ብለው አጥንተው “እናልፋለን፣ ለወላጆቻችንም ሆነ ለሀገራችን እንደርሳለን” ብለው ተስፋ እንዳልሰነቁ እንዳላጠኑ፣ እንዳልደከሙ ወድቀው እንዲቀሩ ያደረጓቸውን ምግባረ ብልሹዎች ማወቅና በታሪክ እንዲወቀሱ፣ በነጠቋቸው የመማር መብት፣ ባጨለሙት ሕይወትም አጥፊዎች ተቀጥተውላቸው ስህተቱ በታናናሾቻቸው ላይ እንደማይደገም ዋስትና ሲሰጥ መስማት ይፈልጉ ነበር::  መምህራንም አስተምረው እንዳላስተማሩ ያስቆጠራቸው ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት ኃላፊነት የጎደለው አሠራር ታርሞ ማዬት ይሹ ነበር:: መንግሥትም ስንት ወጭ እያወጣ ትውልድ ለመገንባት የደከመው ድካም ውኃ እንዲበላው ያደረጉ ግለሰቦችን ለሕግ ማቅረብ ሥራውም ፍላጎቱም ነበር፤ ግን ሆኖ አልሰማንም፤ አላዬንም፤ አላነበብንም፤ ለምን?

እንዲያውም መንግሥት የግዴለሾቹ፣ በትውልድ ዕጣ ፈንታ እየፈረዱ የስንቱን ሕይወት እያጨለሙ ያሉትን አጥፊዎች ጠበቅ አድርጎ ይዞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሲገባው ፈተና እንዳይሠረቅና በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን እንዳይሠራጭ በመፍራት የኢንተርኔት አገልግሎት በአብዛኛው የተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲቋረጥ አደረገ:: አሁን ይኼ ዘዴ ሱሪ ሰጥቶ “እንዳትቀመጥበት” ከማለት በምን ይለያል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ለመረጃ ርሀብ ከማጋለጥና ሀገሪቱንም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማሳጣት በጣት የሚቆጠሩ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያቃታቸውን ወገኖች በጥፋታቸው ልክ ማረም አይሻለውም? ዘላቂ መፍትሔውስ ኢንተርኔት መዝጋት ነው? እንደዚያ ከሆነ በየዓመቱ ፈተና በመጣ ቁጥር ከኢንተርኔት ነፃ ሳምንት እናከብራለን ማለት ነው? እስከ መቼ?

እሺ የፈተና መሰረቁንስ ሥራቸውን ባግባቡ መሥራት ያቃታቸውን  ትቶ ቁም-ነገረኞችን በመቅጣት መቆጣጠር ቻለ እንበል፤  ፈተና አዛብተው የሚያትሙትንና ኃላፊነት ለማይሰማቸው የሚያቀብሉትንስ በምን ሊቆጣጠራቸው ነው?  የዛሬን አይበለውና ተማሪ እያለሁ፣ “ምዘናና አመዛዘን” (‘ሜዠርመንት ኤንድ ኢቫሉዌሺን’ የሚለውን በግርድፍ ተርጉሜው ነው) ስንማር የፈተና አወጣጥ ሥርዓት አለው:: በዚያ ትምህርት መሠረት ፈተና ሲወጣ መጀመሪያ ከትምህርቱ ዓላማ፣ ግብና ውጤት ጋር መጣጣሙና ውስጣዊና ውጫዊ ቅቡልነቱ (ኢንተርናል ኤንድ ኤክስተርናል ቫሊዲቲ) ይፈተሻል:: በመቀጠል ደግሞ የተዘጋጀው ፈተና  የተፈለገውን ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት መለካቱ ይረጋገጣል:: ይህን ለማድረግ በተመረጡና ወካይ በሆኑ ተማሪዎች ላይ ይሞከራል (ቫሊዲቲ ቴስት ይሠራል)::

በዚህ ጊዜ ፈተናው ለሙከራ ሲሰጥ የሚፈጀው ጊዜ፣ የጥያቄው ግልፅነት፣ የጥያቄው እና የመልስ መስጫው ተዛማጅነት፣ የፈተና መለያ ኮዶች ትክክለኛነት፣ ለተማሪያዎች ያለው የችሎታ መዛኝነት (ጎበዝ፣ መካከለኛና ሰነፍ ተማሪዎችን መለዬት መቻል አለመቻሉ) ይፈተሻል:: ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ፣ “ፈተናው በአግባቡ ተዘጋጅቷል፤ መታተም ይችላል” ተብሎ ወደማባዛት የሚኬደው:: ይህ ምዘናና አመዛዘን የሚባል ትምህርት ግን በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት በኩል የሚታወቅ አይመስለኝም:: ይህን ማለቴ የዘንድሮ ፈተና በእነዚህ ሂደቶች ማለፉ ስላጠራጠረኝ ነውና እንደ ድፍረት አትዩብኝ::

ይህንን እንድል ያስቻሉኝ የ10ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ፣ የ12ኛ ክፍል ደግሞ ስነ-ዜጋና ታሪክ ትምህርቶች ታሪካዊ ስህተት ይዘው ለፈተና ስለቀረቡ ነው:: በአንድ የፈተና ጥራዝ ውስጥ የዓመተ ምሕረት፣ የፈተና መለያ ኮድ መለያየት እንዲሁም መዘበራረቅና የጥያቄ ተራ ቁጥር መደገምና መዘለል ተጠቃሽ ስህተቶች ናቸው:: ስህተቶቹ የተፈጠሩት ደግሞ በመጀመሪያው ፈተና በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላይ መሆናቸው ተማሪዎቹ ሌሎች ፈተናዎችን ተረጋግተው እንዳይፈተኑ የሚያደርጉ ጭምር ናቸው::

አማርኛ ቋንቋ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች በመጀመሪያው የፈተና ቀን የወሰዱት ፈተና ነው:: አማርኛ ፈተና ላይ የተፈጠረውን ስህተት የሰማ ተማሪ ቀጣይ ፈተናዎችን ተረጋግቶ ሊሠራ የሚችለው ምን ዓይነት ስነ-ልቦና ቢኖረው ነው? 

አማርኛ ቋንቋ ፈተና ላይ የነበረው የሁለት ጥያቄ መዘለል ስህተት ጉዳቱ ከሁለት ነጥብ በላይ ነው:: ጥያቄው 23 ብሎ ቀጣዩ ተራ ቁጥር 26 ሲሆን በመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ ግን ተራ ቁጥሩ በትክክል ተጽፏል:: በዚህ ምክንያት የ26ኛው ተራ ቁጥር ጥያቄ መልስ በመልስ መስጫ ወረቀቱ ተራ ቁጥር 24 ላይ ይቀመጣል:: በዚህ ሂደት የ90ኛው ተራ ቁጥር ጥያቄ 88ኛው ላይ ያርፋል:: ስለሆነም ተፈታኞች ከተራ ቁጥር 24 ጀምሮ እስከ መጨረሻው የሚሰጡት መልስ በሙሉ ይሳሳታል ማለት ነው::

በዚሁ የአማርኛ ቋንቋ፣ “የፈተና ጥራዝ መለያ ፡- 013” በውስጥ ገጹ እና ከጥራዙ ሽፋን ላይ ደግሞ “Booklet Code: 011” የሚለው ፈተና ላይ በተራ ቁጥር 17 እና 23 የቀረቡ ጥያቄዎች ከምርጫ መልሶች ቅደም ተከተል መለያዬት በቀር ተመሳሳይ ናቸው:: ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከጥራዙ ገጽ 5 ላይ ያለውን ጥያቄ ቁጥር 17 ላስነብባችሁ፡-

“17. ምርጥ ንግግር በምን ይለያል?

A.     ሰፋ ያለ ይዘት በመዳሰስ፤

B.     ሀሳቡን በእንጥልጥል በማስቀረት፤

C.    ለአድማጭ ቁም ነገር በማስጨበጥ፤

D.    አድማጮችን በማደናገር፤”

በገጽ 7 ላይ ደግሞ ጥያቄ ቁጥር 23 እንዲሁ የምርጫ መልሶች ቅደም ተከተል ብቻ ተቀያይሮ መጥቷል፡-

“23. ምርጥ ንግግር በምን ይለያል?

A.     ሀሳቡን በእንጥልጥል በማስቀረት፤

B.     ሰፋ ያለ ይዘት በመዳሰስ፤

C.    አድማጮችን በማደናገር፤

D.    ለአድማጮች ቁም ነገር በማስጨበጥ፤”

እነዚህን መሰል ስህተቶችን የያዘ ፈተና ነው እንግዲህ ለ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኞች የቀረበው::

በዚሁ ፈተና ጥራዝ ላይ በገጽ 5 ያለው ተራ ቁጥር 18 እና ገጽ 7 ያለው ተራ ቁጥር 20 የተቀመጡ ጥያቄዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ ናቸው:: ጥያቄዎቹን በገጻቸው ለመለዬት የፈለግሁት ተራ ቁጥር 17፣ 18፣ 19 እና 20 በድጋሜ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዘው በገጽ 5 እና 6 ላይም ስሚገኙ ነው:: የገጽ 5 ተራ ቁጥር 20 እና ገጽ 7 ያለው ተራ ቁጥር 21 የያዟቸው ጥያቄና መልሶችም አንድ ዓይነት ናቸው:: የገጽ 5 ተራ ቁጥር 19 እና የገጽ 7 ተራ ቁጥር 22 አሁንም አንድ ዓይነት ናቸው:: ከ17 እስከ 20 ያሉት ተራ ቁጥሮች ተደግመው መምጣታቸው በመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ አራት ተጨማሪ የመሳሳቻ ቦታ ስለሚፈጥሩ በዚህ የፈተና መለያ ጥራዝ ቁጥር የተፈተኑ ተማሪዎች ከመጀመሪያው 17ኛ ተራ ቁጥር በኋላ መልስ መስጫ ወረቀታቸው ላይ የሚያሰፍሩት መልስ በሙሉ የተሳሳተ ይሆናል ማለት ነው:: በአጭሩ ተማሪዎቹ በትክክል መሥራት የሚችሉት የኮዱ መለያዬት እንደተጠበቀ ሆኖ የመጀመሪያዎቹን 16 ጥያቄዎች ብቻ ነው::

በሌላ በኩል የአማርኛ ቋንቋ ፈተና መለያ ኮዱ ከሽፋኑ እና በውስጥ ገጾች 6፣ 7፣ 14፣ 15፣ 22 እና 23 ላይ 011 ሲሆን በሌሎች የውስጥ ገጾች 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 8፣ 9፣ 10፣ 11፣ 12፣ 13፣ 16፣ 17፣ 18፣ 19፣ 20፣ 21 እና 24 ላይ ደግሞ መለያ ኮዱ 013 ሆኗል:: ስለዚህ ይህ ፈተና የሚታረመው በየትኛው የፈተና ኮድ ነው:: በነገራችን ላይ ችግር አለበት ከምላችሁ የአማርኝ ፈተና  ጥራዝ መለያ 011 በትክክል የታተመና ስህተት የሌለበትም አለ፤ ይህንን ስመለከት እንዲያውም ስህተቱ ሆን ተብሎ እንደተሠራ ለማሰብ ተገድጃለሁ:: በአንድ የፈተና ኮድ ውስጥ እንዴት የተለያዬ ዓይነት የፈተና አደራደር ሊኖር ይችላል? እኔ እንደሚመስለኝ ፈተናው በትክክል ከተዘጋጀ በኋላ ሆን ብለው በዚያው ኮድ የተሳሳተ የፈተና ጥራዝ አትመው ያስገቡ ተንኮለኞች አሉ ለማለት ያስደፍራል፤ ይሄ ባይሆንማ ኖሮ ሁሉም ስህተት ወይም ሁሉም ትክክል መሆን ነበረበትና ነው ይህን ማለቴ::

ታስታውሱ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በ10ኛ ክፍል የስነ-ዜጋ መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ክልሎች ካርታ በስህተት የተቀመጠበት የመጽሐፍ ገጽ 24 ሁለት ዓይነት ነበር፤ ካርታ ያለውና የሌለው፤ በተመሳሳይ ማተሚያ ቤትና ዓመተ ምሕረት የታተመ:: ዘንድሮ ደግሞ በተመሳሳይ ኮድ የተለያዬ ዓይነት የጥያቄ ስደራ፣ ትክክልና ስህተት ሆነው ታተሙና ለተማሪ ቀረቡ፤ ለምን? ጎበዝ ወደየት እያመራን ነው?  

በመደገምና በመዘለል የመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ የተፈጠሩት መፋለሶች እንዴት ሊታረሙ ይችላሉ? በመጀመሪያው ፈተናቸው ድንብርብራቸው ወጥቶ ሌሎች ፈተናዎችን በአግባቡ ያልሠሩ ተማሪዎች ሕይወትስ በማን ሊቃና ነው? ይህን ዓይነት እንዝህላልነት ያለበት ተቋምስ ትውልድን በትክክል የመቅረጽ ኃላፊነትን ተቀብሎ በሚተጋው መንግሥታችን ዓይን እንዴት ሊይታይ ይሆን? ይህን የመሰለ ተማሪዎችንም ሀገሪቱንም የሚያከስር ፈጽሞ ሊፈጸም የማይገባው ስህተት የተሠራበት  ፈተና ለመፈተን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መውጣትስ ነበረበት? ኢንተርኔትስ  መዘጋት ነበረበት?  በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ተፈታኞች ውጤት መበላሸት ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው? አሁንም በዝምታ ሊታለፍ?  ለምን አጥፊዎች አይጠየቁም?

በዘንድሮው ፈተና ጉድለት ዙሪያ ከአንድ ሙሉ ጋዜጣ በላይ መጻፍ ይቻላል፤ እኔ ግን ትዝብቴን በአጭሩ በዚህ ባበቃ ይሻላል፤ ከስህተቱ ለማይታረም መድከምም አስፈላጊ አልመሰለኝም:: ምክንያቱም የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች በአማራ ቴሌቪዥን በስልክ ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ በስህተታቸው ማዘን፣ ኃላፊነትም መውሰድና ለመታረም መዘጋጀት፣ ሲሆን እንደሰለጠነው ዓለም “ኃላፊነታችንን ባግባቡ አልተወጣንም” ብለው በራሳቸው ላይ መወሰን ሲገባቸው፣ “ጥቃቅን ስህተቶች ስለሆኑ በቀላሉ ተስተካክሎ ይታረማል” ዓይነት ፌዘኛና መራራ መልስ ሲሰጡ ሰምቻለሁ፤ ይሄ በእውነቱ በጣም አስተዛዛቢ ነው:: ጎበዝ ከዚህ በላይ ምን ስህተት ሲሠራ ነው “ጉልህ” የሚባለው? የታሪክና ስነ-ዜጋ ፈተናዎችን ስህተቶች በዝርዝር እናንተው ጥራዞቹን ፈልጋችሁ እንድትመለከቱ ጋብዣለሁ::

በነገራችን ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የ10ኛ ክፍል የታሪክ ትምህርት ሲታረም ስህተት ተሠርቶ እጅግ በርካታ ጎበዝ ተማሪዎች “ኤ” ማግኘት እየቻሉ “ኤፍ” ተብሎ በድረ ገጽ ሲነገራቸው እንደነበረና፤ “እንዴት ይህን ውጤት ልናመጣ እንችላለን?” ብለው ጎበዝ ተማሪዎች ሲጠይቁ “በካርዳችሁ ላይ ተስተካክሎ ይመጣል!” ተብሎ እንደተስተካከለላቸው ታስታውሳላችሁ? እኔ በደንብ አስታውሳለሁ፤ ወንድሜን ጨምሮ በርካታ ጎበዝ ተማሪዎች ስምንት ትምህርቶችን ኤ አግኝተው ታሪክ ኤፍ ሆኖባቸው እንደነበረና እንደተስተካከለላቸው አስታውሳለሁ:: እንዲህ ዓይነት የሰውን ሕይወት የሚያጨልም ስህተት የሚሠራው አካል ግን ይሄን ስህተት የሚሠራው ተግባሩ ምን ቢሆን ነው? ሥራውን በትክክል ለመሥራት ያልቻለውስ ለምንድነው? ያቅም ማነስ? ግዴለሽነት? ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖረው ይሆን? እስኪ በጉዳዩ ላይ ሐሳባችሁን አካፍሉን::

June 20, 2017

Pages

Visitors

  • Total Visitors: 3051299
  • Unique Visitors: 184022
  • Published Nodes: 2537
  • Since: 03/23/2016 - 08:03