Bekur Amharic

Deatail:

 

ባህር ዳር፡ ሰኔ 13 /2009 ዓ/ም (አብመድ)“ከስህተቱ የማይማር ፈንጅ አምካኝ ብቻ ነው” የሚል ጥቅስ ከዓመታት በፊት ታክሲ ውስጥ ማንበቤን አስታውሳለሁ:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ጥቅሱን በደንብ አብላላሁት:: ከዚያም፣ “ፈንጅ አምካኝ ለምን ከስህተቱ አይማርም?” ብዬ ራሴን ጠየኩ:: በኋላ ራሴ ለራሴ መልስ ሰጭ ሆንኩና፣ “ፈንጅ አምካኝ ስህተት ከሠራ ስህተቱ ሕይወቱን ስለሚያጠፋው ከስህተቱ የሚማርበት ዕድል የለውም፤ አባባሉ የሚያስረዳው ይሄንን እውነታ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ::

አሁን ደግሞ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት የሚባል ከስህተቱ የማይማር፣ ነገር ግን ስህተቱ ያላጠፋው፤ በተደጋጋሚ በሚሠራው ስህተት ትውልድን የሚያጠፋ ተቋም እያዬን ነው:: ይሄ ተቋም ባለፈው ዓመት በፈፀመው ስህተት የፈተና ወረቀቶች ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች እጅ ገብተው በማኅበራዊ ድረ ገፆች በመለቀቃቸው የፈተናው ጊዜ ተራዘመ፤ የተማሪዎች ስነ-ልቦና ክፉኛ ተጎዳ፤ ተማሪዎቹ በራስ መተማመን እንደራቃቸው ማኅበራዊ ድረ ገፆች ተዘግተውና በይድረስ ይድረስ ፈተና ተዘጋጅቶ ተፈተኑ፤ (ትምህርት ሚኒስቴር “በመጠባበቂያነት የተዘጋጀውን ፈተና ነው ያቀረብኩት” ብሎ የነበረ ቢሆንም::

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለፈተና የተቀመጡ የአማራ ክልል የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት አስመዘገቡ:: ለፈተና ከተቀመጡት ውስጥ የማለፊያ ነጥብ ያላገኙት (የወደቁት ለማለት ያልደፈርኩት ተፈታኞች የወደቁት በእነሱ ስህተት መሆኑን ስላላመንኩበት ነው) 67 ነጥብ 51 ከመቶ ሆኑ:: ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተማሪዎችን በማሳለፍ ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ተርታ ተሰለፈ::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ “ጥናት አካሄድኩ” ብሎ ያወጣው የውጤት ትንተና የሚያሳዬው ምክንያቶቹ፡- “የተማሪዎች የመማር ፍላጎት መቀነስ፣ መምህራን ለተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጋቸው፣ የወላጆች ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆን፣ በቂ የትምህርት ግብዓት አለመሟላት፣ የፈተና አፈታተን ችግር (ሌላ ቦታ ፈተና በመሰረቁ ወይም የተሳሳተ መልስ  በመሠራቱ)፣ የማለፊያ ነጥቡ ከፍ ማለቱ፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜ መባከንና የትምህርት ይዘት አለመሸፈን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መኖር” እንደሆኑ ነው::

እንደኔ ትዝብት ግን ለችግሩ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት፣ “የአፈታተን ችግር (ሌላ ቦታ ፈተና በመሰረቁ ወይም የተሳሳተ መልስ በመሠራቱ)” የሚለው ነው:: ከዚያ ውጭ ያሉት የትምህርት ቢሮው የፈጠራቸው ሰበቦች የፈተና አዘጋጁንና የአስተዳዳሪውን አካል ለመሸፈን የቀረቡ የሚመስሉ የማያሳምኑ ሰንካላ ምክንያቶች ናቸው:: ይህ ግን “ችግሮቹ የሉም” ማለት አይደለም:: እንዲያውም የተጠቀሱት  በአብዛኛው በፊት ጎልተው ይስተዋሉ የነበሩ፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው:: የመምህራን ለተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረግ በየዓመቱ የሚነሳ ችግር እንደሆነ እናውቃለን:: ያንን ችግር ለማቃለል ብሎም ለመፍታት መንግሥት በየጊዜው መምህራንን ለማበረታት የሚወስደውን እርምጃም እናውቃለን፤ የመምህራንን መታተርም ከአንደበታቸው እንሰማለን:: ታዲያ እንዴት 32 በመቶ ብቻ ተማሪ ለማሳለፍ ይህ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል?

እንዲያው ምንም መቀባባት ሳያስፈልገው ባለፈው ዓመት ያ ሁሉ ተማሪ የወደቀው የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጉና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ፈተናው ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች እጅ በመግባቱና በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በመለቀቁ የተማሪዎች ስነ-ልቦና በመጎዳቱ የተነሳ ነው:: ሌሎቹ ምክንያቶች ምክንያት ቢሆኑም የዚህን ያክል የውጤት ማሽቆልቆል አያስከትሉም ነበር፤ ምክንያቱም በየዓመቱ የነበሩና እየተቃለሉ የመጡ ችግሮች ናቸውና::

የሚገርመው ነገር ያንን ያህል የስነ-ልቦና ቀውስ በተማሪዎች ላይ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑ ስህተት ፈጻሚዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መቀጣት አለመቀጣታቸው ወይም የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው ስለመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አለመገለፁ ነው:: ወላጅ ስንት ለፍቶ፣ “የነገ ተስፋ ይሆኑኛል፤ ሕይወቴን ይለውጡልኛል፤ እነሱም የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ” ብሎ ያስተማራቸው  ልጆቹ ውጤት እንዲበላሽ ምክንያት የሆኑ ሰዎች በጥፋታቸው ሕግ ፊት ቀርበው ሲቀጡ ሕዝቡ ማየትም ሆነ መስማት ይፈልግ ነበር:: ተማሪዎች ስንት ደክመው ተምረው፣ ዓመቱን ሙሉ ቀን ከሌሊት ድፍት ብለው አጥንተው “እናልፋለን፣ ለወላጆቻችንም ሆነ ለሀገራችን እንደርሳለን” ብለው ተስፋ እንዳልሰነቁ እንዳላጠኑ፣ እንዳልደከሙ ወድቀው እንዲቀሩ ያደረጓቸውን ምግባረ ብልሹዎች ማወቅና በታሪክ እንዲወቀሱ፣ በነጠቋቸው የመማር መብት፣ ባጨለሙት ሕይወትም አጥፊዎች ተቀጥተውላቸው ስህተቱ በታናናሾቻቸው ላይ እንደማይደገም ዋስትና ሲሰጥ መስማት ይፈልጉ ነበር::  መምህራንም አስተምረው እንዳላስተማሩ ያስቆጠራቸው ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት ኃላፊነት የጎደለው አሠራር ታርሞ ማዬት ይሹ ነበር:: መንግሥትም ስንት ወጭ እያወጣ ትውልድ ለመገንባት የደከመው ድካም ውኃ እንዲበላው ያደረጉ ግለሰቦችን ለሕግ ማቅረብ ሥራውም ፍላጎቱም ነበር፤ ግን ሆኖ አልሰማንም፤ አላዬንም፤ አላነበብንም፤ ለምን?

እንዲያውም መንግሥት የግዴለሾቹ፣ በትውልድ ዕጣ ፈንታ እየፈረዱ የስንቱን ሕይወት እያጨለሙ ያሉትን አጥፊዎች ጠበቅ አድርጎ ይዞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሲገባው ፈተና እንዳይሠረቅና በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን እንዳይሠራጭ በመፍራት የኢንተርኔት አገልግሎት በአብዛኛው የተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲቋረጥ አደረገ:: አሁን ይኼ ዘዴ ሱሪ ሰጥቶ “እንዳትቀመጥበት” ከማለት በምን ይለያል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ለመረጃ ርሀብ ከማጋለጥና ሀገሪቱንም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማሳጣት በጣት የሚቆጠሩ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያቃታቸውን ወገኖች በጥፋታቸው ልክ ማረም አይሻለውም? ዘላቂ መፍትሔውስ ኢንተርኔት መዝጋት ነው? እንደዚያ ከሆነ በየዓመቱ ፈተና በመጣ ቁጥር ከኢንተርኔት ነፃ ሳምንት እናከብራለን ማለት ነው? እስከ መቼ?

እሺ የፈተና መሰረቁንስ ሥራቸውን ባግባቡ መሥራት ያቃታቸውን  ትቶ ቁም-ነገረኞችን በመቅጣት መቆጣጠር ቻለ እንበል፤  ፈተና አዛብተው የሚያትሙትንና ኃላፊነት ለማይሰማቸው የሚያቀብሉትንስ በምን ሊቆጣጠራቸው ነው?  የዛሬን አይበለውና ተማሪ እያለሁ፣ “ምዘናና አመዛዘን” (‘ሜዠርመንት ኤንድ ኢቫሉዌሺን’ የሚለውን በግርድፍ ተርጉሜው ነው) ስንማር የፈተና አወጣጥ ሥርዓት አለው:: በዚያ ትምህርት መሠረት ፈተና ሲወጣ መጀመሪያ ከትምህርቱ ዓላማ፣ ግብና ውጤት ጋር መጣጣሙና ውስጣዊና ውጫዊ ቅቡልነቱ (ኢንተርናል ኤንድ ኤክስተርናል ቫሊዲቲ) ይፈተሻል:: በመቀጠል ደግሞ የተዘጋጀው ፈተና  የተፈለገውን ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት መለካቱ ይረጋገጣል:: ይህን ለማድረግ በተመረጡና ወካይ በሆኑ ተማሪዎች ላይ ይሞከራል (ቫሊዲቲ ቴስት ይሠራል)::

በዚህ ጊዜ ፈተናው ለሙከራ ሲሰጥ የሚፈጀው ጊዜ፣ የጥያቄው ግልፅነት፣ የጥያቄው እና የመልስ መስጫው ተዛማጅነት፣ የፈተና መለያ ኮዶች ትክክለኛነት፣ ለተማሪያዎች ያለው የችሎታ መዛኝነት (ጎበዝ፣ መካከለኛና ሰነፍ ተማሪዎችን መለዬት መቻል አለመቻሉ) ይፈተሻል:: ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ፣ “ፈተናው በአግባቡ ተዘጋጅቷል፤ መታተም ይችላል” ተብሎ ወደማባዛት የሚኬደው:: ይህ ምዘናና አመዛዘን የሚባል ትምህርት ግን በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ድርጅት በኩል የሚታወቅ አይመስለኝም:: ይህን ማለቴ የዘንድሮ ፈተና በእነዚህ ሂደቶች ማለፉ ስላጠራጠረኝ ነውና እንደ ድፍረት አትዩብኝ::

ይህንን እንድል ያስቻሉኝ የ10ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ፣ የ12ኛ ክፍል ደግሞ ስነ-ዜጋና ታሪክ ትምህርቶች ታሪካዊ ስህተት ይዘው ለፈተና ስለቀረቡ ነው:: በአንድ የፈተና ጥራዝ ውስጥ የዓመተ ምሕረት፣ የፈተና መለያ ኮድ መለያየት እንዲሁም መዘበራረቅና የጥያቄ ተራ ቁጥር መደገምና መዘለል ተጠቃሽ ስህተቶች ናቸው:: ስህተቶቹ የተፈጠሩት ደግሞ በመጀመሪያው ፈተና በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላይ መሆናቸው ተማሪዎቹ ሌሎች ፈተናዎችን ተረጋግተው እንዳይፈተኑ የሚያደርጉ ጭምር ናቸው::

አማርኛ ቋንቋ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች በመጀመሪያው የፈተና ቀን የወሰዱት ፈተና ነው:: አማርኛ ፈተና ላይ የተፈጠረውን ስህተት የሰማ ተማሪ ቀጣይ ፈተናዎችን ተረጋግቶ ሊሠራ የሚችለው ምን ዓይነት ስነ-ልቦና ቢኖረው ነው? 

አማርኛ ቋንቋ ፈተና ላይ የነበረው የሁለት ጥያቄ መዘለል ስህተት ጉዳቱ ከሁለት ነጥብ በላይ ነው:: ጥያቄው 23 ብሎ ቀጣዩ ተራ ቁጥር 26 ሲሆን በመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ ግን ተራ ቁጥሩ በትክክል ተጽፏል:: በዚህ ምክንያት የ26ኛው ተራ ቁጥር ጥያቄ መልስ በመልስ መስጫ ወረቀቱ ተራ ቁጥር 24 ላይ ይቀመጣል:: በዚህ ሂደት የ90ኛው ተራ ቁጥር ጥያቄ 88ኛው ላይ ያርፋል:: ስለሆነም ተፈታኞች ከተራ ቁጥር 24 ጀምሮ እስከ መጨረሻው የሚሰጡት መልስ በሙሉ ይሳሳታል ማለት ነው::

በዚሁ የአማርኛ ቋንቋ፣ “የፈተና ጥራዝ መለያ ፡- 013” በውስጥ ገጹ እና ከጥራዙ ሽፋን ላይ ደግሞ “Booklet Code: 011” የሚለው ፈተና ላይ በተራ ቁጥር 17 እና 23 የቀረቡ ጥያቄዎች ከምርጫ መልሶች ቅደም ተከተል መለያዬት በቀር ተመሳሳይ ናቸው:: ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከጥራዙ ገጽ 5 ላይ ያለውን ጥያቄ ቁጥር 17 ላስነብባችሁ፡-

“17. ምርጥ ንግግር በምን ይለያል?

A.     ሰፋ ያለ ይዘት በመዳሰስ፤

B.     ሀሳቡን በእንጥልጥል በማስቀረት፤

C.    ለአድማጭ ቁም ነገር በማስጨበጥ፤

D.    አድማጮችን በማደናገር፤”

በገጽ 7 ላይ ደግሞ ጥያቄ ቁጥር 23 እንዲሁ የምርጫ መልሶች ቅደም ተከተል ብቻ ተቀያይሮ መጥቷል፡-

“23. ምርጥ ንግግር በምን ይለያል?

A.     ሀሳቡን በእንጥልጥል በማስቀረት፤

B.     ሰፋ ያለ ይዘት በመዳሰስ፤

C.    አድማጮችን በማደናገር፤

D.    ለአድማጮች ቁም ነገር በማስጨበጥ፤”

እነዚህን መሰል ስህተቶችን የያዘ ፈተና ነው እንግዲህ ለ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኞች የቀረበው::

በዚሁ ፈተና ጥራዝ ላይ በገጽ 5 ያለው ተራ ቁጥር 18 እና ገጽ 7 ያለው ተራ ቁጥር 20 የተቀመጡ ጥያቄዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ ናቸው:: ጥያቄዎቹን በገጻቸው ለመለዬት የፈለግሁት ተራ ቁጥር 17፣ 18፣ 19 እና 20 በድጋሜ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዘው በገጽ 5 እና 6 ላይም ስሚገኙ ነው:: የገጽ 5 ተራ ቁጥር 20 እና ገጽ 7 ያለው ተራ ቁጥር 21 የያዟቸው ጥያቄና መልሶችም አንድ ዓይነት ናቸው:: የገጽ 5 ተራ ቁጥር 19 እና የገጽ 7 ተራ ቁጥር 22 አሁንም አንድ ዓይነት ናቸው:: ከ17 እስከ 20 ያሉት ተራ ቁጥሮች ተደግመው መምጣታቸው በመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ አራት ተጨማሪ የመሳሳቻ ቦታ ስለሚፈጥሩ በዚህ የፈተና መለያ ጥራዝ ቁጥር የተፈተኑ ተማሪዎች ከመጀመሪያው 17ኛ ተራ ቁጥር በኋላ መልስ መስጫ ወረቀታቸው ላይ የሚያሰፍሩት መልስ በሙሉ የተሳሳተ ይሆናል ማለት ነው:: በአጭሩ ተማሪዎቹ በትክክል መሥራት የሚችሉት የኮዱ መለያዬት እንደተጠበቀ ሆኖ የመጀመሪያዎቹን 16 ጥያቄዎች ብቻ ነው::

በሌላ በኩል የአማርኛ ቋንቋ ፈተና መለያ ኮዱ ከሽፋኑ እና በውስጥ ገጾች 6፣ 7፣ 14፣ 15፣ 22 እና 23 ላይ 011 ሲሆን በሌሎች የውስጥ ገጾች 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 8፣ 9፣ 10፣ 11፣ 12፣ 13፣ 16፣ 17፣ 18፣ 19፣ 20፣ 21 እና 24 ላይ ደግሞ መለያ ኮዱ 013 ሆኗል:: ስለዚህ ይህ ፈተና የሚታረመው በየትኛው የፈተና ኮድ ነው:: በነገራችን ላይ ችግር አለበት ከምላችሁ የአማርኝ ፈተና  ጥራዝ መለያ 011 በትክክል የታተመና ስህተት የሌለበትም አለ፤ ይህንን ስመለከት እንዲያውም ስህተቱ ሆን ተብሎ እንደተሠራ ለማሰብ ተገድጃለሁ:: በአንድ የፈተና ኮድ ውስጥ እንዴት የተለያዬ ዓይነት የፈተና አደራደር ሊኖር ይችላል? እኔ እንደሚመስለኝ ፈተናው በትክክል ከተዘጋጀ በኋላ ሆን ብለው በዚያው ኮድ የተሳሳተ የፈተና ጥራዝ አትመው ያስገቡ ተንኮለኞች አሉ ለማለት ያስደፍራል፤ ይሄ ባይሆንማ ኖሮ ሁሉም ስህተት ወይም ሁሉም ትክክል መሆን ነበረበትና ነው ይህን ማለቴ::

ታስታውሱ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በ10ኛ ክፍል የስነ-ዜጋ መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ክልሎች ካርታ በስህተት የተቀመጠበት የመጽሐፍ ገጽ 24 ሁለት ዓይነት ነበር፤ ካርታ ያለውና የሌለው፤ በተመሳሳይ ማተሚያ ቤትና ዓመተ ምሕረት የታተመ:: ዘንድሮ ደግሞ በተመሳሳይ ኮድ የተለያዬ ዓይነት የጥያቄ ስደራ፣ ትክክልና ስህተት ሆነው ታተሙና ለተማሪ ቀረቡ፤ ለምን? ጎበዝ ወደየት እያመራን ነው?  

በመደገምና በመዘለል የመልስ መስጫ ወረቀቱ ላይ የተፈጠሩት መፋለሶች እንዴት ሊታረሙ ይችላሉ? በመጀመሪያው ፈተናቸው ድንብርብራቸው ወጥቶ ሌሎች ፈተናዎችን በአግባቡ ያልሠሩ ተማሪዎች ሕይወትስ በማን ሊቃና ነው? ይህን ዓይነት እንዝህላልነት ያለበት ተቋምስ ትውልድን በትክክል የመቅረጽ ኃላፊነትን ተቀብሎ በሚተጋው መንግሥታችን ዓይን እንዴት ሊይታይ ይሆን? ይህን የመሰለ ተማሪዎችንም ሀገሪቱንም የሚያከስር ፈጽሞ ሊፈጸም የማይገባው ስህተት የተሠራበት  ፈተና ለመፈተን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መውጣትስ ነበረበት? ኢንተርኔትስ  መዘጋት ነበረበት?  በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ተፈታኞች ውጤት መበላሸት ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው? አሁንም በዝምታ ሊታለፍ?  ለምን አጥፊዎች አይጠየቁም?

በዘንድሮው ፈተና ጉድለት ዙሪያ ከአንድ ሙሉ ጋዜጣ በላይ መጻፍ ይቻላል፤ እኔ ግን ትዝብቴን በአጭሩ በዚህ ባበቃ ይሻላል፤ ከስህተቱ ለማይታረም መድከምም አስፈላጊ አልመሰለኝም:: ምክንያቱም የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች በአማራ ቴሌቪዥን በስልክ ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ በስህተታቸው ማዘን፣ ኃላፊነትም መውሰድና ለመታረም መዘጋጀት፣ ሲሆን እንደሰለጠነው ዓለም “ኃላፊነታችንን ባግባቡ አልተወጣንም” ብለው በራሳቸው ላይ መወሰን ሲገባቸው፣ “ጥቃቅን ስህተቶች ስለሆኑ በቀላሉ ተስተካክሎ ይታረማል” ዓይነት ፌዘኛና መራራ መልስ ሲሰጡ ሰምቻለሁ፤ ይሄ በእውነቱ በጣም አስተዛዛቢ ነው:: ጎበዝ ከዚህ በላይ ምን ስህተት ሲሠራ ነው “ጉልህ” የሚባለው? የታሪክና ስነ-ዜጋ ፈተናዎችን ስህተቶች በዝርዝር እናንተው ጥራዞቹን ፈልጋችሁ እንድትመለከቱ ጋብዣለሁ::

በነገራችን ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የ10ኛ ክፍል የታሪክ ትምህርት ሲታረም ስህተት ተሠርቶ እጅግ በርካታ ጎበዝ ተማሪዎች “ኤ” ማግኘት እየቻሉ “ኤፍ” ተብሎ በድረ ገጽ ሲነገራቸው እንደነበረና፤ “እንዴት ይህን ውጤት ልናመጣ እንችላለን?” ብለው ጎበዝ ተማሪዎች ሲጠይቁ “በካርዳችሁ ላይ ተስተካክሎ ይመጣል!” ተብሎ እንደተስተካከለላቸው ታስታውሳላችሁ? እኔ በደንብ አስታውሳለሁ፤ ወንድሜን ጨምሮ በርካታ ጎበዝ ተማሪዎች ስምንት ትምህርቶችን ኤ አግኝተው ታሪክ ኤፍ ሆኖባቸው እንደነበረና እንደተስተካከለላቸው አስታውሳለሁ:: እንዲህ ዓይነት የሰውን ሕይወት የሚያጨልም ስህተት የሚሠራው አካል ግን ይሄን ስህተት የሚሠራው ተግባሩ ምን ቢሆን ነው? ሥራውን በትክክል ለመሥራት ያልቻለውስ ለምንድነው? ያቅም ማነስ? ግዴለሽነት? ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖረው ይሆን? እስኪ በጉዳዩ ላይ ሐሳባችሁን አካፍሉን::

June 20, 2017

Pages

Visitors

  • Total Visitors: 1440396
  • Unique Visitors: 92854
  • Published Nodes: 1596
  • Since: 03/23/2016 - 08:03