ፌዴራል ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የያዛቸው 100 የብራና መጽሐፍትን ለቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስረከበ

ባህር ዳር፡ ጥቅምት 1/2010 ዓ/ም (አብመድ)የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከተለያዩ ገዳማትና አድባራት ተዘርፈው በግለሰቦች ሲዘዋወሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ 100 ጥንታዊ የብራና መጽሐፍትን ተረከበ።

በአገሪቷ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ተመዝግበው ባለማለቃቸው ለቅርስ ክትትልና ቁጥጥር ስራው እንቅፋት መሆኑ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ተነስቷል።Image may contain: 1 person

በ1992 ዓ.ም በወጣው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ አዋጅ መሰረት በአባቶች አገር በቀል ዕውቀት ከዕጽዋት ቀለም በመቀመም በቆዳ ላይ በመጻፍ የሚዘጋጁት የብራና መጽሐፍትን ለመስራት ብዙ ዋጋ የሚጠይቅና የዕውቀቱ መሰረት የሆኑ አባቶች ቁጥራቸው እየተመናመኑ በመምጣታቸው መጽሀፍቱ በተንቀሳቃሽ ቅርስነት ተመዝግበዋል።

አዋጁ እነዚህንም ሆነ ሌሎች ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን አግባብነት ካለው ፈቃድ ተይዞ ካልሆነ በአገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጪ ማንቀሳቀስ እንደማይቻልም ይደነግጋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ "የአገር በቀል ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን አስመስሎ በመስራት የአገር በቀል እውቀት፣ ታሪክ፣ ባህልና የኑሮ ዘይቤ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚበረታታ ቢሆንም አንዳንድ የስጦታ ዕቃ አምራቾችና ሻጮች ግን ቅርሶችን አስመስሎ በመስራት ቱሪስቶችን የማታለል ተግባር እየፈጸሙ ነው" ብለዋል።

በዚህም ብራናዎችን ጨምሮ የአገሪቷ ቅርሶች እንዲጠፉና መለየት እንዳይቻል ተደርገው ከአገር እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ አናጋው እንዳሉት በዕለቱ ርክክብ የተፈጸመባቸው የብራና መጽሐፍትም አዘዋዋሪዎቹ ወደ ውጭ ለማስወጣት በሚሞክሩበት ወቅትና በስጦታ ዕቃ መሸጫዎች በፍተሻ የተያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቅርሶቹ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ምርመራ ሲደረግባቸው የቆዩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ቅርሶቹ ከሶስት ግለሰቦች እጅ የተያዙ ሲሆን ከአንደኛው ተጠርጣሪ 2፣ከሁለተኛው ተጠርጣሪ 33 እንዲሁም ከሶስተኛው ተጠርጣሪ 65 በድምሩ 100 ብራናዎች ተይዘዋል ብለዋል።

ቅርሶቹም ለፍርድ ቤት ቀርበው ተገቢውን ውሳኔ ካገኙ በኋላ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መመለሳቸውን ነው ያብራሩት።

ከተመለሱት የብራና መጽሐፍት መካከል ወንጌላት፣ ድርሳናት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ አዕማደ ምስጢራት፣ መጽሐፈ ክርስትና፣ መጽሐፈ ድጓ ይገኙበታል።

ብራናዎቹ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተቀምጠው ለጥናትና ምርምር አገልግሎት የሚውሉ ሲሆን ቅርሶቹ የተመዘገቡ ከሆነ ተጣርቶ ላስመዘገቡ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት እንደሚመለሱ ተገልጿል።

ፖሊስ የኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ባለቤትነቷን የሚገልጹ ብራናዎቸን ጨምሮ፣ አደገኛ አደንዛዠ ዕፆችና የዱር እንስሳት አካል አዘዋዋሪ ግልሰቦችን በህግ ተጠያቂ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ህብረሰተቡ በህገ ወጥ ተግባራት ተሳታፊ አካላት እንዲጠቁም ጠይቀዋል።

የባለስልጣኑ የቅርስ ምዝገባ፣ቁጥጥርና ደረጃዎች ምደባ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው የቅርስ ምዝገባ የቅርሶችን አይነት፣ ብዛት፣ የጉዳት መጠን ለመለየት፣ ቁጥጥር ለማድረግ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማዋል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይሁንና የቅርስ ባለይዞታ ተቋማትና ግለሰቦች ቅርሶችን የማስመዝገብ ኃላፊነት ባለመወጣታቸው ለቅርስ ክትትልና ቁጥጥር ስራው እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።

በመሆኑም የኋይማኖት ተቋማት የቅርስ ማስመዝገብን ፋይዳ ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ የማስተማርና የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ኢዜአ ባደረሰን መረጃ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን መመዝገብ የተቻለ ሲሆን በአጠቃላይ ግን 500 ሺህ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን መመዝገብ እንደሚጠበቅ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 2964590
  • Unique Visitors: 182434
  • Published Nodes: 2537
  • Since: 03/23/2016 - 08:03