ጆርጅ እና አማል ክሉኒ 3 ሺ የሶሪያ ስደተኛ ህጻናትን ትምህርት ቤት ሊያስገቡ ነው

ባህር ዳር፡ ሐምሌ 26/2009 ዓ/ም (አብመድ)ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ እና ባለቤቱ አማል ክሉኒ በሺዎች ለሚቆጠሩ የሶሪያ ስደተኞች የትምህርት ወጪ በመሸፈን ለማስተማር መወሰናቸውን ሲ ኤን ኤን ዘገበ ፡፡

የክሉኒ ፋውንዴሽን ለፍትህ የሚል ድርጅት የመሠረቱት ጥንዶች ከዩኒሴፍ እና ጎግል ጋር በመተባበር ሊባኖስ ውስጥ ለሚገኙ ሰባት የህዝብ ትምህርት ቤቶች 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር የመደቡ ሲሆን ኤች ፒ የተባለው የኮምፒውተር አምራች ኩባንያ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማቅረብ ተስማምቷል ፡፡

ፋውንዴሽኑ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ከመክፈት ይልቅ ያሉት ትምህርት ቤቶች የማስተማሪያ ሰዓታቸውን እንዲያራዝሙ እና ዘመናዊ የትምህርት መርጃዎች እንዲሟሉላቸው ያደርጋል ተብሏል ፡፡

 

በሊባኖስ የሶሪያ ስደተኞችን የሚያስተምሩ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ሁለት ፈረቃ እንዳላቸው የገለጹት የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ላውረን ዳቪት የሊባኖስ ተማሪዎች የጥዋቱን ፈረቃ ሲይዙ የከሰዓት በኋላውን ደግሞ ስደተኞች ይጠቀሙበታል ብለዋል ፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ከ 5 ሚሊዮን በላይ የሶሪያ ስደተኞች በዓለም ዙሪያ ተበትነው የሚኖሩ ሲሆን ከ 1 ሚሊዮን የሚበልጡት ሊባኖስ ውስጥ ይገኛሉ ፡፡ እንደ ዩኒሴፍ ግምት ሊባኖስ ውስጥ ወደ 2 መቶ ሺ የሚደርሱ የሶሪያ ስደተኛ ህጻናት የትምህርት ዕድል አላገኙም ፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3300939
  • Unique Visitors: 189354
  • Published Nodes: 2588
  • Since: 03/23/2016 - 08:03