ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰሩ በአማራ፣ኦሮምያ እና በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ የጸጥታ አካላት ተናገሩ፡፡

ባህር ዳር፡ ጥቅምት 1/2010 ዓ/ም (አብመድ)የጸጥታ ዘርፍ አመራሮች በምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር እና ጸጥታ ጉዳዮች መምሪያ አዘጋጅነት በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል፡፡ 
በአማራ፣ኦሮምያ እና በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተጠናከረ የቁጥጥር ስርዓት እና በጸጥታ አካላት የእርስ በርስ ግንኙነት መላላት ምክንያት በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡


ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእነዚህ ክልሎች አስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ አካላት በየጊዜው እየተገናኙ በቅንጅት መስራት በመጀመራቸው የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቀንሰዋል፡፡ ከሁለቱም ከልሎች ጋር የሚዋሰነው የምዕራብ ጎጃም ዞንም ከአዋሳኝ ዞኖች የጸጥታ እና አስተዳደር ዘርፍ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ 


ተሳታፊዎቹም የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች የወንጀል ተግባራትን በጋራ በሚከላከሉበት ሂደት ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ለ2010 ዓ/ም በጀት ዓመት እቅድ ወጥቶም ተወያይተውበታል፡፡ 


የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር እና ጸጥታ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ አበባው ውቤ አቅዱ የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያስተሳስር እና ለጸጥታ ተግባር ጠቀሜታው ጎላ ነው ብለዋል፡፡


የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ በበኩላቸው የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ፣ምስራቅ ጎጃም ፣አዊ እና ደቡብ ጎንደር፣ ከኦሮምያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም የሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ደግሞ የከማሸ ዞን የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይም በየ ሦስት ወሩ ተመሳሳይ የምክክር መድረኮችን ለማካሄድ ተስማምተዋል፡፡
አብዮት ከፋለ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3433575
  • Unique Visitors: 194891
  • Published Nodes: 2605
  • Since: 03/23/2016 - 08:03