የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አደረገ

ባህርዳር፡ጥር 02 /2010 ዓ/ም(አብመድ)የህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ /ህወሓት/ ጥልቅ ተሃድውን ተከትሎ የትግራይ ክልል ምክር ቤት እያካሔደ ባለው አስቸኳይ ጉባኤው የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ከነበሩበት ኃላፊነት በማንሳት ወደ ሌላ ስራ እንዲመደቡ ወሰነ።

የክልሉ ህገ-መንግስት በሚፈቅደው መሰረትም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር እስኪሾም ድረስ በምትካቸው ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሆነው እንዲመሩ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ አባላትን ሹመት እያካሄደ ያለው ነባሩ የህወሓት አመራር ስትራቴጂክ ሆኖ መምራት አለመቻሉን በግምገማው መለየቱን ተከትሎ ነው፡፡

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  ታህሳስ 2/2010 ዓ.ም ይፋ ባደረገው አዲስ  ምደባ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ ዶክተር አዲስአለም ባሌማና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በትግራይ ክልል እንዲሰማሩ፤ አቶ ዓለም ገብረዋህድና አቶ ጌታቸው ረዳ በህወሓት ዋና ጽህፈት ቤት ተመድበው እንዲሰሩ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የክልሉ ህገ መንግሥት የምክር ቤቱ አባል ያልሆነ አመራር በርዕሰ መስተዳድርነት መሾም እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

ዶክተር ደብረ ጽዮንም   የክልሉ ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው ነው የርዕሰ መስተዳድርነት ሹመቱን ያላገኙት፡፡

ይሁን እንጂ የርዕሰ መስተዳድሩን ኃላፊነት ተክተው እንደሚሰሩና የክልሉን መንግሥት ካቢኔም እንደሚመሩ ተመልክቷል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ቃለመሃላ  ፈጽመው አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበው አስጸድቀዋል፡፡

በዚህም መሰረት ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የካቢኒ አባል፣ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ፣  አቶ ዳንኤል አሰፋ የፋይናንስና እቅድ ቢሮ ሀላፊ፣ አቶ ተክላይ ገብረመድህን የሰሜናዊ ምእራብ ትግራይዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም አቶ ማሞ ገብረእግዚአብሄር የማዕከላዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾመዋል፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3527358
  • Unique Visitors: 199328
  • Published Nodes: 2627
  • Since: 03/23/2016 - 08:03