የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቶምቦላ መውጫ ቀን ተራዘመ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቶምቦላ ሎተሪ መውጫ ቀን መራዘሙን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
 
ጽሕፈት ቤቱ ከብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ "አንድ ቶምቦላ ሎተሪ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ" በሚል መሪ ቃል የቶምቦላ ሎተሪ ትኬት ገቢያ ላይ መዋሉ ይታወሳል።
 
የሎተሪው ዕጣ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚወጣ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ትኬቱ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎችና ተቋማት ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመድረሱ መውጫው ቀን ለ10 ቀናት እንዲራዘም ተደርጓል።
 
የጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ዛሬ በሰጡት መግለጫ የሎተሪ ትኬቱ በአንዳንድ የአገሪቱ የአካባቢዎችና ተቋማት እንዲሁም ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች በበቂ ሁኔታ አልደረሰም።
 
በመሆኑም የዕጣው መውጫ ቀን እንዲራዘም በተቋማቱና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀረበው ጥያቄ መሰረት ለቀጣይ 10 ቀናት እየተሸጠ እንዲቆይ ተወስኗል ብለዋል።
 
የቶምቦላ ሎቶሪው ሽልማቶችን ያካተተና አገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ሽያጩ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ህብረተሰቡ የቶምቦላ ሎተሪውን በመግዛት ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
 
ዕጣው ሰኔ 10 ቀን 2009 ዓ.ም የሚወጣ ሲሆን ከሎተሪ ሽያጩ በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
 
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ በተጨማሪ በህዳሴ ዋንጫና በሌሎችም የገቢ ማሰባሰበቢያ መንገዶች እስካሁን ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል ይላል የጽህፈት ቤቱ መረጃ።

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3284008
  • Unique Visitors: 188934
  • Published Nodes: 2588
  • Since: 03/23/2016 - 08:03