የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ቦኮ ሀራምን ለመዋጋት ሃይላቸውን አቀናጁ፡፡

ባህርዳር፡ጥር 05 /2010 ዓ/ም(አብመድ)ካሜሩን፣ኒጀር እና ቻድ ከናይጄሪያ ጋር እንደገና ሃይላቸውን በማቀናጀት አሸባሪውን ቡድን ቦኮሃራምን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአካባቢው ለማስወገድ ቆርጠው መነሳታቸውን ሲጂቲኤን ዘገበ ፡፡

ጠንካራው  ቡጢ /ዲፕ ፓንች -2 / በሚል መጠሪያ በቻድ ሸለቆ ውስጥ ቅንጅት በመፍጠር የሚንቀሳቀሱት አራቱ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የአሸባሪውን ቡድን ዱካ ተከታትለው ለመደምሰስ  መቆማቸውን አስታውቀዋል ፡፡

በሰሜናዊ ናይጄሪያ ሳምቢሳ ደን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የቦኮሃራም አሸባሪ ቡድን በአቡበክር ሼካው የሚመራ ሲሆን በቻድ ሃይቅ አካባቢ ያለውን ጠንካራ ይዞታ የሚመራው ደግሞ ማማን ኑር የተባለ ታጣቂ ነው ፡፡

ይህ ሰው የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን በመምራት ከአቡበክር ሼካው ቀጥሎ አደገኛ እየሆነ መምጣቱን መረጃው ያመለክታል ፡፡  

በአሸባሪው ቦኮሃራም ቡድን ላይ እስካሁን ከተደረጉት የማጥቃት ዘመቻዎች መካከል ስኬታማ ተብሎ የተሞገሰው ባለፈው ሳምንት የጦር ሃይሉ በአየር እና በምድር ባደረገው ውጊያ 1ሺ 50 ታጣቂዎች እጅ የሠጡበት ክስተት ነው ፡፡

በዚህ ዘመቻ የታወቀ የቦኮ ሀራም ከፍተኛ አመራር ባለቤትን ጨምሮ 107 ታጣቂዎች በጥቃቱ እንደተገደሉ ሪፖርቱ ጨምሮ አብራርቷል ፡፡

ዘመቻውን በድል ያጠናቀቀው የናይጄሪያ መንግስት በአሸባሪው ቡድን ላይ ያደረሰውን ወታደራዊ ኪሳራ ይፋ በማድረግ የተማረኩ ከባድ የጦር መሳሪያዎች እና የተደመሰሱ ንብረቶችን ለህዝብ ዓይንና ጆሮ ማድረሱ ተዘግቧል ፡፡

ቀደም ብሎ አራቱ የክልሉ ተጎራባች ሃገራት ቦኮሃራምን ለመደምሰስ በጋራ ቢቆሙም በገንዘብ እጥረት ምክኒያት ጸንተው መዝለቅ አለመቻላቸውን መረጃው አመልክቷል ፡፡       

 

 

 

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3433358
  • Unique Visitors: 194890
  • Published Nodes: 2605
  • Since: 03/23/2016 - 08:03