የላልይበላ ማር ሙዚየም ዛሬም ስራ አልጀመረም

 

ባህር ዳር፡ ነሀሴ 1/2009 ዓ/ም (አብመድ)የላልይበላ ማር ሙዚየም በ2000 ዓ.ም የግንባታ መሠረት ድንጋይ ሲቀመጥለት በአጭር ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ይገባል የሚል ዕቅድ ተይዞለት ነበር:: ነገር ግን  ግንባታው የተጀመረው ከተባለው ጊዜ ዘግይቶ   በ2003 ዓ.ም ነው:: ከክልሉ መንግሥት በተመደበ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በአማራ ህንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የግንባታ ሥራው ተከናውኖ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ተጠናቅቋል::

 

የላልይበላ የማር ሙዚየምን  ለመገንባት ሲታሰብ ዋና ዓላማው በላስታና በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የማር ሀብት ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ገበያ እንዲያገኝ በማድረግ  የማር አምራች ገበሬዎችን  ህይወት መለወጥ ነው:: ከዚህ ባለፈም በማር ምርት ዙሪያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣትና ጥናትና ምርምር ማድረግ የሙዚየሙ ተግባር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል:: በውስጡ የማር ምርትን ወደ እሴት ሰንሰለት በማስገባት ኤክስፖርት የማድረግ  ሰፊ ሥራዎች እንደሚከናወኑበት የታሰበ ሲሆን ለዚሁ ተግባር የሚሆን ከ80 ሄክታር በላይ ጥብቅ ሥፍራን  ለንብ ማነቢያነት አካቷል:: ነገር ግን ይህ ሙዚየም ለ10 ዓመታት ከመጓተቱም በላይ በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚችል የጐላ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም:: ይህ ደግሞ ሙዚየሙን ተስፋ ባደረጉ የማር አምራች ገበሬዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል:: ለመሆኑ የአካባቢው የማር ምርት እንቅስቃቄ ምን ፈተናዎች አሉበት? የሙዚየሙ ሚናስ ምን ይሆን ነበር? አሁን ያለበት ደረጃና የወደፊት ተስፋውስ ምንድን ነው? በዚህ ትንታኔ እንመለከታቸዋለን::

 

ደብረ ሎዛ ተብሎ በሚጠራውና በላስታ ወረዳ ሰሜናዊ አቅጣጫ በሚገኘው ቀበሌ የሚኖሩት ንብ አናቢው ቄስ መላኩ በዛ የፀሀይ ሙቀት ከመበረታቱ በፊተ የጓሯቸውን የማር ቀፎ መቃኘት ይኖርባቸዋል:: ማለዳ ላይ ንቦቹ ብዙ እንቅስቃሴ ሥለማያደርጉ ቄስ መላኩ ቀፏቸውን ለማጽዳት ምቹ ጊዜ ይሆንላቸዋል:: ይህንን ካከናወኑ በኋላም ወደ እርሻ ማሣቸው ያመራሉ:: እንዲህ አይነቱ ተግባር በቄስ መላኩ ዘንድ በየዕለቱ ይከናወናል::

ቄስ መላኩ የንብ ማነብ ሥራን የተማሩት ከአባታቸው ነው:: አንድ የቀንድ ከብት ሸጠው ሁለት የንብ ቀፎ በመግዛት የጀመሩት የንብ ማነብና የማር ምርት ሥራ ዛሬ ላይ ከ70 በላይ ቀፎዎች ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: እርሳቸው የሚኖሩበትን አካባቢ ጨምሮ በሰሜናዊና ሞቃታማው የኢትዮጵያ ክፍል ከንብ ጋር ኑሯቸውን ያስተሳሰሩ ገበሬዎች ይገኛሉ::

 

ከእነዚህ አካባቢዎች ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብ የማር ምርትም ከፍተኛ ተቀባይነት አለው:: ብዙዎች ለላስታ ማር ጣዕምና ልዩ ኃይል አድናቆት አላቸው::

ቄስ መላኩ በዛ እንደሚሉት የአካባቢው የማር ምርት ከሌሎች ለየት የሚያደርገው የአካባቢው ስነ ምህዳር ምቹነት ነው:: በቁጥቋጦና በተፈጥሮ ደን የተሞሉት የላስታና አካባቢው ተራሮች የዚህ ሚስጢር ባለቤቶች ናቸው:: በተለይም በአካባቢው መንጠሴ እየተባለ የሚጠራው የቁጥቋጦ አይነት የንቦች ተመራጭ ቀሰም በመሆኑ የሚሠሩትን ማር ልዩ ጣዕምና መልክ ይሠጠዋል:: አብዛኛውን ጊዜም በዚህ አካባቢ የሚመረተው ማር ነጭ በሆነው ቀለሙ ይታወቃል:: ቄስ መላኩ ይህንን የማር አይነት 70 በሚደርሡ ቀፎዎቻቸው ያመርቱታል:: “በአካባቢያችን ሁለት አይነት ማር ነው የምናመርተው:: ቀዩ ማር ብዙ ቦታ የሚመረት አይነት በመሆኑ በዋጋው ቀነስ ይላል:: ነጩ ግን በገበያ በጣም ተፈላጊ ነው” ይላሉ::

ንብ አናቢው ቄስ መላኩ በዓመት ከ100 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ከቀፏቸው ይቆርጣሉ:: ብዛት ያለውን ምርትም ለገበያ እንደሚያቀርቡ ነው የሚገልፁት:: ነገር ግን ገበያው ብዙ ውጣ ውረድ አለበት ይላሉ::

 

“ምርታችንን የምንሸጠው ላልይበላ ከተማ ሄደን ነው:: ማሩን ተሸክመን ልክ እንደ እህል ገበያ ቁጭ ብለን በችርቻሮ እንሸጠዋለን:: ጥሩ ገበያ ካለ ከ100 እና ከ150 ብር በላይ በኪሎ እንሸጣለን:: ነገር ግን ምርታችንን አንድ ጊዜ የሚረከበን ነጋዴ ወይም ሌላ አካል ስለሌለ ለጉብኝት የሚመጡ ሰዎች ናቸው የሚገዙን:: አልፎ አልፎ ነጋዴዎች ሲመጡ ደግሞ በደላላ ዋጋውን እንዲቀንስ አድርገው ይገዙናል:: በአጠቃላይ ገበያ ድረስ ማር ተሸክሞ ሄዶ መሸጥ በጣም አድካሚ ነው:: የልፋታችንን ያህል አልተጠቀምንም” ይላሉ::

 

እነ ቄስ መላኩ ከዓመታት በፊት የላልይበላ የማር ሙዚየም ይገነባል ሲባል አንድ ተሥፋ ይዘው ነበር:: ሙዚየሙ የማር ምርትን እያቀነባበረ ወደ ውጭ ገበያ ስለሚያቀርብ  በሙዚየሙ የተሻለ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ግምት ነበራቸው:: ነገር ግን ይህ ተሥፋ መዘግየቱ ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል:: “ሙዚየሙ ስራ ቢጀምር ኖሮ ምርታችንን አንድ ጊዜ ማስረከብ እንችል ነበር:: የገበያ ውጣ ውረድም አይገጥመንም:: ከዚህ ባለፈ ጠንካራ ማኅበራት እንዲፈጠሩና ህጋዊ የማር ምርት ግብይት እንዲኖር ያግዛል:: ሆኖም በጣም ዘግይቶብናል” ብለዋል::

 

በላስታና አካባቢው በየዓመቱ የሚመረተውን ከ400 ቶን በላይ የማር ምርት በብዛት ተረክቦና እሴት ጨምሮ ወደ ግብይት ለማውጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ እጅግ ደካማ ነው:: ከዓመታት በፊት ይህንን ምርት መረከብ ጀምሮ የነበረው የጥረት ኮርፖሬት አካል የሆነው የየጁ ማር እሸት ድርጅት ከአንድ ዓመት በላይ መረከብ አልቻለም:: በአሁኑ ወቅት በትንሹም ቢሆን እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የላል ማር እሸት የንብ ውጤቶች ልማት ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው:: 170 የማር አምራች ገበሬዎችን ያቀፈው ይህ ማኅበር የማር ምርትን አጣርቶና አሽጐ ለሀገር ውስጥ እና አልፎ አልፎ ለውጭ ገበያ ያቀርባል::

 

አቶ ተገኘ ሽፈራው የማኅበሩ ጸሐፊ ናቸው:: እርሳቸው አንደሚሉት በአካባቢው የሚሰበሰበው የማር ምርት ከተፈላጊነቱ አንፃር ያለው ግብይት በቂ አይደለም:: ማኅበሩም ይህንን ክፍተት ብቻውን ሊሸፍን እንደማይችልና ተጨማሪ የማቀነባበሪያ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ያምናሉ:: በዚህ ረገድ ተሥፋ ተጥሎበት የነበረው የማር ሙዚየም ሥራ ቢጀምር ኖሮ የአምራች ገበሬዎችንና የአነስተኛ ማኅበራትን ምርት በመረከብ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር ብለዋል::

ማርን እንደ መስህብ ለማስተዋወቅ፣ በንብ እርባታ ዙሪያ የሚደረግን እንቅስቃሴ በምርምር ለመደገፍና ከማር ምርት የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብና መጠጦችን ለማስተዋወቅ አዲስ መንገድ ይዞ ይመጣል የተባለው የላልይበላ ማር ሙዚየም ላለፉት 10 ዓመታት በግንባታ ሂደት ላይ ነው የቆየው::

ምንም እንኳ በዚህ ዓመት ግንባታው የተጠናቀቀ ቢሆንም ቶሎ ወደ ሥራ መግባት ግን አልቻለም:: በቀን ከስምንት ኩንታል በላይ የማር ምርት ማቀነባበር እንደሚችል ሲነገርለት የቆየው ሙዚየሙ ትናንት ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የላስታ የንብ አናቢ ገበሬዎች ተስፋ ቢሆንም ዛሬ ላይ ስድስት የኮንስትራት ጥበቃ ሰራተኞችን ከመቀጥርና አዳራሹን ለስብሰባ ከመጠቀም ባለፈ ምንም እንቅስቃሴ አያደርግም::

ሙዚየሙን በጊዜያዊነት እያሰተዳደረ የሚገኘው የላስታ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽ/ቤትም “ሙዚየሙን በጊዜያዊነት ከማስተዳደር ባለፈ ምንም ሥልጣን የለኝም” ብሏል:: የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ደጀን ሙዚየሙን በበላይነት የሚያስተዳድረው የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት  ማስፋፊያ ኤጀንሲ በመሆኑ “የእኛ ድርሻ ደህንነቱን የማስከበር ሥራ ብቻ ነው” ብለዋል::

ጉዳዩን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ዘሪሁን ሙዚየሙ አብዛኛውን ጊዜ በግንባታ ሂደት ላይ የነበረ በመሆኑ አገልግሎቱ ዘግይቷል ሊባል እንደማይችል ገልፀዋል:: በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ሙዚየሙን ለማስተዳደር በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ደንብ አውጥቶ ለክልሉ መንግሥት ካቤኔ ያቀረበ ሲሆን መጽደቁን እየተጠባበቀ ይገኛል ብለዋል:: ለዚህም የሚያስፈልገው የሰው ኃይል መለየቱንም የተናገሩት ምክትል ስራ አስኪያጁ ደንቡ እንደፀደቀ ለሲቪል ሰርቪስ ተልኮ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል::

ከዚህ በተጨማሪም ለሙዚየሙ የሚያስፈልጉት የቴክኖሎጅ መሣሪያዎች ከደንቡ መጽደቅ በኋላ ተገዝተው እንደሚተከሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል:: ነገር ግን ካቤኔው ደንቡን መቼ ሊያፀድቅ እንደሚችል መገመት አልችልም ነው ያሉት::

በአጠቃላይ ሙዚየሙ በዚህ ጊዜ አገልግሎት ይጀምራል ብሎ መናገር ቢከብድም የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ጊዜ ለአገልግሎት ክፍት ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል::

አብርሃም አዳሙ

 

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537655
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03