እስራኤል በዌስት ባንክ የምትገነባውን አጥር አጠናቀቀች

ባህር ዳር፡ ሐምሌ 27/2009 ዓ/ም (አብመድ)እስራኤል በምስራቃዊ ዌስት ባንክ የፍልስጤም ከተማ በሆነችው አልካሊል ከተማ (ሄብሮን) አቅራቢያ ያለውን አወዛጋቢ የመለያ አጥር ገንብታ ማጠናቀቋን አስታወቀች፡፡ የእስራኤል ወታደራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደገለጸው ታርኩሚያ እና ሚታር በሚባሉት የፍልስጤም መንደሮች ውስጥ 42 ኪሎ ሜትር የአጥር ግንባታ ተጠናቋል ብሏል፡፡

የደቡባዊ ሂብሮን የግምብ አጥር መጠናቀቅ እየጨመረ የመጣውን የከተማዋ ነዋሪዎች ደኅንነት ስጋት ለመታደግ ትልቅ መፍትሄ ይሆናል ያሉት የወታደራዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቪግዶር ሊበርማን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጸጥታ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል ፡፡ ምንም እንኳ እስራኤል የአጥር ግንባታው ፕሮጀክት በግዛቶቿ ውስጥ የሚፈጠሩትን የጸጥታ ችግሮች ለመከላከል ነው ብትልም ፍልስጤም ግን የመብት ጥሰት ተፈጽሞብኛል በማለት እየከሰሰች ነው ፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ መሠረት ግንባታው 9.4 በመቶ የሚሆነውን የዌስት ባንክ ፣ የምስራቅ ኢየሩሳሌምንና አልቁዳ የተሰኙትን ክልሎች ይነካል ፡፡ ዓለም አቀፉ ፍርድቤት የግንብ አጥሩ ሰብአዊ መብትን የሚጥስ ነው በሚል እስራኤል ከድርጊቱ እንድትታቀብ እ.ኤ.አ. በ2014 ቢያሳስብም ተቀባይ አላገኘም ፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ. ከ1967ቱ ጦርነት በኋላ ፍልስጤማውያንን እያፈናቀለች ነው የሚል ዓለምአቀፍ ወቀሳ ቢሠነዘርባትም ስድስት መቶ ሺ ዜጎቿን በ230 የሰፈራ መንደሮች ውስጥ አስፍራለች፡፡ አሁንም መርሃግብሯን እየገፋችበት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ እስራኤል እ.ኤ.አ. ከ2002 ጀምሮ በዌስት ባንክ 712 ኪ.ሜ የግምብ አጥር እየገነባች ትገኛለች፡፡ ምንጭ፡-ፕሬስ ቲቪ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3300943
  • Unique Visitors: 189354
  • Published Nodes: 2588
  • Since: 03/23/2016 - 08:03