ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ

ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ 

 146 times
ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ
 

ባህርዳር፡ጥር 02 /2010 ዓ/ም(አብመድ)ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሱዳን ኢታማጆር ሹም ሌተናንል ጄኔራል ኢማን አልዲን አዳዊን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው  አነጋግረዋል።

ኢታማጆር ሹሙ ከፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የተላከውን መልዕክትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢታማጆር ሹሙ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና በቀጠናው ባሉ አገራት ጉዳዮችም መክረዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን የገለጹት ሌትናል ጄኔራሉ፤ አገራቱ በቀጣይ የጋራ ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

አንዱን አገር የሚያጋጥም ፈተና ሁለቱን አገር እንደሚጎዳ ገልጸው፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመግታት የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የሁለቱ አገራት የአብሮነት ስሜትና የትብብር መንፈስ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረ ወዲህ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዴሊቨሪ ዩኒት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብረሃ ናቸው።

በዛሬው ውይይትም ይህ ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚሸጋገርበት ሁኔታ ላይ እንዳተኮረ ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የሁለቱን አገራት ብሔራዊ ጥቅምና የቀጠናውን ጥቅም ለማስከበር በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ በጋራ የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አገራቱ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አቶ ዛድግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ወዳጅነታቸውን በየጊዜው በማጠናከር ላይ ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት  ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አገራቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት መፍጠር፣ ለጋራ ሰላም አብሮ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3537545
  • Unique Visitors: 199679
  • Published Nodes: 2652
  • Since: 03/23/2016 - 08:03