ታንዛኒያ ህብረተሰቡ ከሰል እንዳይጠቀም ልትከለክል ነው፡፡

ባህርዳር፡ጥር 05 /2010 ዓ/ም(አብመድ)በከሰል አምራቾች እና በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ የከሰል ነጋዴዎች አማካኝነት እየተፈጸመ ያለውን ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ በማስቆም ህብረተሰቡ እ.ኤ.አ ከ2025 ጀምሮ ከሰል ከመጠቀም እንዲታቀብ የታንዛኒያ መንግስት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ሺንዋ ዘግቧል ፡፡  

እንደ ዋና ከተማዋ ዳሬሰላም ባሉ ታላላቅ ከተሞች ውስጥ የሃይል ፍላጎትን ለማሟላት በመቶ ሺዎች የሚገመት ሔክታር ደን አስደንጋጭ በሆነ መንገድ በክሰል አምራች እና ህገወጥ ነጋዴዎች አማካኝነት እየተጨፈጨፈ ሲሆን ይህ ድርጊት በጊዜ ሂደት ካልተገታ ከሃገርም በላይ አለም አቀፍ ተጽዕኖ ይፈጥራል ሲል መንግስት እርምጃውን ለመውሰድ ተገዷል፡፡

የሃገሪቱ የኃይል እና ማዕድን ሚኒስቴር እንደገለፀው ዳሬሰላም በየቀኑ ከበርካታ የእግር ኳስ ሜዳዎች ጋር እኩል ስፋት ያለው የደን ሽፋን ትጠቀማለች ብሏል፡፡ይህ ደግሞ በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡

በመንግስት እገዳ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የአንድ ጆንያ ከሰል ዋጋ ከፍተኛ ሆኗል የሚለው የከሰል ነጋዴ ኢሻካ ሳሉም የደኑም መመናመን አሳስቦኛል ብሏል ፡፡

ታንዛኒያ በዓለም ላይ ከፍተኛ የከሰል ተጠቃሚ ህዝብ ያለባት ሃገር ስትሆን ከሰል ዋነኛው የሃይል ምንጭ ነው፡፡

በየዓመቱ በታንዛኒያ ሁለት ሚሊዮን ቶን ከሰል ጥቅም ላይ እንደሚውል ሺንዋ ጠቅሶ ከዚህ ውስጥ በዳሬሰላም ብቻ ግማሽ ያህሉ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስታውቋል ፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3527353
  • Unique Visitors: 199328
  • Published Nodes: 2627
  • Since: 03/23/2016 - 08:03