ቤተ ክርስቲያኗ የላሊበላን ቅርሶች ከጉዳት ለማዳን ጥሪ አቀረበች፡፡


ባህር ዳር: ህዳር 12/2010 (አብመድ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከጉዳት ለመታደግ ሁሉን አቀፍ እርዳታ መጠየቋን የቅርስ እንክብካቤ እና የቱሪዝም ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገለጹ፡፡ 
ቤተክርስቲያኗ የአለም ሃብት የሆኑትን የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከጉዳት ለማዳን ከሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን ችግሮችን ለማስወገድ የበኩሏን እየሰራች መሆኗን የገለጹት በቤተክርስቲያኗ የቅርስ እንክብካቤ እና የቱሪዝም ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ቄስ ሰለሞን ቶልቻ ናቸው፡፡

እንደዳይሬክተሩ መግለጫ ከአስር አመት በፊት በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ቅርሱን ከጸሃይና ዝናብ ለመከላክል የተገነባው መጠለያ ከማዳን ይልቅ በቅርሱ ላይ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ የከፋ አደጋ ከመድረሱ በፊት መጠለያውን ለማስወገድ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ቅርሱንም ጠብቆ ለማቆየት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቅርቡ ስራውን ለማስጀመር ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም ወደ 800 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ታውቋል ፡፡
በዚህም መሠረት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ቅርሱን ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂስቶች እና ሌሎች የውጭ አገር ባለሙያዎች በቅርሱ ጥበቃ ላይ ያላቸውን ጥናት አቅርበው ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ለጉዳት የዳረገውን መጠለያም ለማፍረስም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል ቄስ ሰለሞን ቶልቻ ፡፡

በመጨረሻም መገናኛ ብዙሃን፣የመንግስት አካላትና ሌሎች ድርጅቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳዩትን ርብርብ አሁንም በቅርስ ማዳን ተግባርም ላይ ሊደግሙት ይገባል ሲሉ ቄስ ሰለሞን ቶልቻ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢትዮጵያን ሄራልድን ጠቅሶ ኦል አፍሪካ ዘግቧል ፡፡ 
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ጥንታዊ ቅርሶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ለ 800 ዓመታት ያህል በአስደናቂነቱ ጎብኚዎችን እያስደመመ መንፈሳዊ አገልግሎትም በመስጠት ላይ ይገኛል ፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3870117
  • Unique Visitors: 214834
  • Published Nodes: 2859
  • Since: 03/23/2016 - 08:03