በጭስ እያፈኑ ደንበኛን ማማለል i

ባህርዳር፡ጥር 25/2010 ዓ/ም(አብመድ)ወጣት አንለይ በለጠ ይባላል፡፡በባህዳር ከተማ ቀበሌ 14 በተለምዶ አውስኮድ አደባባይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለባለፉት አምስት ዓመታት ጫማ በማሳመር ይተዳደር ነበር፡፡ወጣቱ ከጠዋት 1 ሰዓት ተኩል ጀምሮ እስከ ምሽት 1 ሰዓት ድረስ ስራ ቦታው ላይ ይገኛል፡፡
በማንኛውም ሰዓት የሄደ ሰው አያጣውም፡፡ እርሱም በርካታ ደንበኞች አሉት እና ስራውን ደስ እያለው ይስራል፡፡አሁን አሁን ግን ለአንለይ ስራ አስቸጋሪ የሆነ ጤና መታወክ ችግር አጋጥሞታል ፡፡ አፍንጫውን ስለሚያፍነው መተንፈስ ያሰቸግረዋል፡፡
ሆኖም ግን ለአንደዚሀ አይነት በሽታ ከሚያጋልጡ ስራዎች መካከል የአንለይ ስራ አንዱ ነውና እሱን ምክንያት ማድረጉ አልቀረም፡፡

በተለይ ወደ ምሽት አካባቢ ከቅዝቃዜው ጋር ተዳምሮ የሚያስቸግረው አፍንጫ መታፈን በየጊዜው እየባሰበት ይሄዳል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ሁሌ የለመደው ነገር ግን የሚሰነፍጥ ሽታ በድንገት ያፍነዋል፡፡የተቃጠለ ስጋ ሽታ ነው፡፡
ይህ ክስተት ሁሌም ወደ ማታ የሚያጋጥመው ነው፡፡ትኩረት ግን ሰጥቶት አያውቅም፡፡በዚህ ቅጽበት የየትኛው ስጋ ቤት ሽታ እንደሆነ ከተቀመጠበት ተነስቶ ተመለከተ፡፡

ዋና መንገዱን ግራና ቀኝ ይዘው የተደረደሩ ከአስር ያላነሱ ስጋቤቶች ከፊት ለፊታቻው እሳትና ጭስ የሚተፉ ተንቀሳቃሽ የብረት ምድጃዎች አጅበዋቸው ያስተውላል፡፡ወዲያው አንለይ የአፍንጫው መታፈን ችግር ገባውና ከመቼ ጀምሮ እንዳመመው ወደ ሁዋላ ማሰብ ጀመረ፡፡በአካባቢው ለአምስት ዓመት ይስራ እንጅ የአፍንጫ መታፈን ችግር የገጠመው ግን በአንድ ዓመት ውስጥ ነው ፡፡


ወጣቱም ሽታው ስላስቸገረው ከቀበሌ 14 ወደ መሀል ከተማ ጊዮርጊስ አካባቢ የስራ ቦታውን በመቀየር ከማይጠገበው የጣና ነፋሻማ አየር እየተቋደሰ ጫማውን ያሳምራል፡፡እኔም ጫማየን ለማፀዳት አዲስ ደንበኛ ሆኘ ተዋወቅን፡፡

እናም ወጣት አንለይ ያወራኝን ትዝብት መነሻ በማድረግ በባህርዳር ከተማ ያሉ ስጋ ቤቶች ማሰብ ጀመረኩ፡፡
አሁን አሁን ከስጋ ውጭ ምግብ ከቢራ ውጭ መጠጥ የለም የተባለ ይመስል የሰፈር መኖሪያ ቤቶች እንኳ ሳይቀሩ ዘርፋቸውን ወደ ስጋ ቤት የቀየሩ የትየለሌ ናቸው፡፡

ጸሀይ ውሎዋን ጨርሳ ጊዜዋን ለጨረቃ ልታስረክብ ሸለብለብ ሲያደረጋት እኔም ከወጣት አንለይ የተቀበለኩትን ትዝብት በመያዝ በዛ ያለ የስጋ ቤት ቁጥር ወዳለቸው ሰፈሮች መዘዋወሬን ቀጠልኩ፡፡

መጀመሪያ ወደ ቀበሌ 14 ከኖክ ነዳጅ ማደያ እስከ አውስኮድ አደባባይ ባሉት ሰፈሮች አመራሁ፡፡በአካባቢው ወደ 12 የሚጠጉ መጠጥና ስጋ ቤቶች ግራና ቀኝ ሞቅ ባለ መልኩ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡አብዛኛቹ ስጋ ቤቶች ፊት ለፊት በተንቀሳቃሽ ምድጃ ላይ የተንቀለቀለ እሳት ይተፋሉ፡፡በዚህ የተነሳ አካባቢው ከየትኛው ስጋ ቤት እንደመጣ በማይለይ የስጋ ጠረን የሸክላ ጥብሰ አምሮትን ያስጎመዣል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የሚቀረና ጠረን በድንገት አፍንጫን ይሰነፍጣል፡፡

ወደ መረጥኩት ስጋ ቤት ጠጋ ብየ ባለ ስጋቤቱን ለምን የስጋ ተረፈ ምርት በተለይ አጥንት እና ነጭ ስጋ እንደሚያቃጥሉ ጠየኩት፡፡ 
ባለ ስጋቤቱም “እንዴ ካምፋየር እኮ ነው፡፡ ምርጥ ደንበኛ መሳቢያ ዘዴ፡፡አንተም ዝም ብለህ አልመጣህም ወይ የቋንጣ አልያም የሸክላ ጥብስ ጠረን ማርኮህ ነው” አለኝ፡፡ 
ታዲያ ሽታው አይጎዳም? አልኩት፡፡ “ይህ ምን ይጎዳል ብለህ ነው? ሽታው ሰውን በጣም ስለሚማርከው እያማረው ሳይበላ ቢሄድ የሚያመው ይመስለዋል፡፡ ለዚህ ነው ይህ ሁሉ በአካባቢው የምታይው ምድጃ ሲለኝ እውነታውን የበለጠ ለማረጋገጥ መሃል ከተማ ፓፒረስ ሆቴል ፊት ለፊት ባሉት ስጋ ቤቶች ቃኘሁ፡፡ያ የተለመደ ተንቀሣቃሽ ምድጃ በየስጋ ቤቱ በር ላይ አጥንት ይቃጠልበታል፡፡

አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የስጋ ቤት ባለቤት ይህን የሚያደርጉት ለደንበኛ መሣቢያ መሆኑን ገልፆ ይህ ባይሆን ግን ደንበኛው ብዙ ጊዜ ወደ ቤት ይዞት የሚሄደው ስጋ እንጂ እዛው ገዝቶ እንደ ማይመገብ ይናገራል፡፡ለባለ ስጋ ቤቶቹ ደግሞ እዛው ገዝቶ መመገቡ የበለጠ ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡የሰውን የስጋ ፍላጐት ለመጨመር የግድ የስጋ ተረፈ ምርት ማቃጠል እንዳለበት አምኖ ጭሱ/ሽታው/ ግን የሰውን ጤንነት እንደሚጐዳ ይናገራል፡፡

እኔም ደንበኞችን ማናገሬን ቀጠልኩ አቶ ምንተስኖት አባተ የተባሉት ግለሰብ አልፎ አልፎ ስጋ ቤቶች አካባቢ እንደሚመጡ ተናግረው ሽታው የበለጠ የመብላት ፍላጐት እንደሚያመጣ ሲናገሩ በተለይ የማቅለሽለሽ ባህሪይ ያለባቸውን ሰዎች እንደሚያስጐመዥ ከልምዳቸው ያዩት መሆኑን ገልፀውልኛል፡፡

በዚህ መነሻ የስጋ ተረፈ ምርት ማቃጠል በተለይ በአካባቢው በቋሚነት በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምን ችግር ያስከትል ይሆን? ስል በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የህክምና አገልግሎት አስተባባሪ ለዶ/ር ሞላ ገደፋው ጥያቄየን አቀረብኩ፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ ‹‹የስጋ ተረፈ ምርት ማቃጠል ለአካባቢው ኗሪዎችና መንገደኞች የጉንፋንና አስም በሽታ ዋና መንስኤ ይሆናል፡፡ በተለይም ለህፃናትና ነፍሰጡር እናቶች ጉዳቱ የበለጠ ነው፡፡ማቅለሽለሽና ራስ ምታት ጨምሮ ለትውከት ሊዳርጋቸው ይችላል›› ብለዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ሲያጋጥም የመተንፈሻ ችግር ሊሆን ስለሚችል ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደለባቸው መክረዋል፡፡

በምሽት አካባቢ ስጋቤቶች የስጋ ተረፈ ምርት ማቃጠላቸው ከጤና ችግር ባለፈ ጭሱን ለመሸሽ ሲባል ሰዎችና ተሽከርካሪዎች ለግጭት እንደሚዳርግ የተናገሩት ደግሞ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት የጥናትና ስልጠና ባለሙያ አቶ መብራቴ ቢምረው ናቸው፡፡ አቶ መብራቴ አክለውም ህብረተሰቡን ሊያውኩ የሚችል ስራ መስራትም ሆነ በመንገድ ዳር የስጋ ተረፈ ምርት ማቃጠል በህግ የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡

ድርጊቱን ፈጽሞ የተገኘ ግለሰብ እስከ 2 ሺህ 6 መቶ ብር ያስቀጣል፡፡ ድርጅት ከሆነ ደግሞ 3 ሺህ ብርና ንግድ ፈቃድ እስከ መነጠቅ ያደርሳል ብለዋል፡፡ በመንገድ ላይ ይህን ሥራ የሚሠሩ ግለሠቦችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሣስበዋል፡፡

በአደራው ምንውየለት የተዘጋጀ ነው፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3300968
  • Unique Visitors: 189355
  • Published Nodes: 2588
  • Since: 03/23/2016 - 08:03