በደሴ ከተማ ወሃን በማሸግ ዘይት አስመስሎ ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦች በአስራት ተቀጡ፡፡

ባህር ዳር: ህዳር 13/2010(አብመድ)በደሴ ከተማ አስተዳደር የ1ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ባለሙያ የሆኑት ዋ/ሣጅን ሰፊው ገደፋየ እንደገለፁት በዘይት ጀሪካን ውሃ በማሸግ ዘይት አስመስሎ የመሸጡ ድርጊት የተፈፀመው በከተማ አስተዳደሩ ፒያሳ ክፍል ከተማ አራዳ ተብሎ ከሚጠራው አከባቢነው፡፡

ድርጊቱን የፈፀሙት ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ ፀጋየ ብርሃኔ፣ 2ኛ ተከሳሽ ዋካ ኃይሌ፣ 3ኛ ተከሳሽ ሹሻይ አዲስ ዓለም የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

አታላዩቹ ባለ ሃያ ሊትር የዘይት ጀሪካን በጐኑ በመቅደድ ውሃ ከሙሉ በኋላ ጀሪካኑን በማቃጠል ያሽጉታል፡፡ ድርጊቱም እንዳይታወቅባቸው የትክክለኛ ዘይቶችን መለያ አርማን እንዳይለቅ በማድረግ ለጥፈውበት ሲሸጡ መቆየታቸውን የወንጀል ምርመራ ባለሙያው ዋና ሣጅን ሰፊው ገደፋየ አስረድተዋል፡፡

ዋና ሳጅን ጨምረው እንደገለፁት የችግሩ ገፈት ቀማሽ አንድ ግለሰብ ከአታላዬቹ ባለ 20 ለትር 3 ጀሪካንን በእርካሽ ዋጋ በ2250 ብር ገዝተው ወደ እቤት ከወሰዱ በኋላ ሲከፈት የገዙት ዘይት ሳይሆን ውሃ ሆኖ ያገኙታል፡፡

ወዲያ ለፖሊስ ባደረጉት ጥቆማ መሰረት አታላዬቹ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲጣራባቸው መቆየቱን ዋ/ሣጅን ሰፊው ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድም መዝገቡን በማስረጃዎች በማጠናከር ወደ ሚመለከተው የፍትህ አካል ልኳል፡፡ ከፖሊስና አቃቢ ህግ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብን የተመለከተው የደሴ ከተማ አስተዳደር የደ/ወሎ ዞን ከፍተኛው ፍ/ቤት የተከሳሹቹን ጥፋተኝነት በልዩ ልዩ ማስረጃ አረጋግጧል፡፡

በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ፀጋ ብርሃኔ፣ ሁለት ዓመት ከ3 ወር እስራት፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ተከሳሾች ዋካ ኃይሌና ሹሻይ አዲስ አለም ሁለት ዓመት ከስድት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ፍ/ቤቱ ሦስቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል ሲል ከደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሪፖርተራችን ቢኒያም በላይ ዘግቧል፡፡

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3693148
  • Unique Visitors: 209286
  • Published Nodes: 2809
  • Since: 03/23/2016 - 08:03