በያዘችው የእድገት አቅጣጫ ከተጓዘች መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ቅርብ ነው ፡-ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

ባህር ዳር፡ መስከረም 30/2010 ዓ/ም (አብመድ)የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ 2ኛ አመት የስራ ዘመን አንደኛ የጋራ መደበኛ ጉባኤ ሲከፈት በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ለሞቱ ሰዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

 ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ሃገሪቱ ለ15 አመታት ያክል በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ እድገት ማስመዝገቧን በማስታወስ  በ2009 ዓ.ም. በነበራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ 10.9 በመቶ እድገት አስመዝግባለች ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱ ምክር ቤቶች እንደተናገሩት ሃገሪቱ አሁን በያዘችው የእድገት አቅጣጫ ከተጓዘች መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለዋል፡፡

 

ባለፉት አመታት ሃገሪቱ በድርቅ ብትጠቃም በኢንዱስትሪ ዘርፉ እና በአገልግሎት ዘርፉ አማካኝነት 8.2 በመቶ እድገት እንድታስመዘግብ የረዳት መሆኑ የሚታወስ ነው ብለዋል ፕሬዘዳንት ሙላቱ በሪፖርታቸው፡፡

 

እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ከሆነ በ2009 በኢኮኖሚ ዘርፍ 11.1 በመቶ ለማስመዝገብ ታቅዶ የተሰራ ሲሆን በግብርና ዘርፉ ላይ በነበረው ክፍተት እና ፈጣንና ሁሉን አውዳሚ ተምች ባስከተለው ችግር ምክንያት 36 ከመቶ ኢኮኖሚውን የሚደግፈውን ግብርና ቢጎዳውም በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፉ ላይ የተሰራው ስራ ኢኮኖሚው 10.9 በመቶ እንዲያስመዘግብ አድርጎታል ብለዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ 36 በመቶ ኢንዱስትሪው 26 በመቶ ከዚህ ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ 6.4 በመቶ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ  33.3 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል ፡፡

 

በቀጣዩ 2010 ዓ›ም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 7 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ የሚሰራ ሲሆን የአነስተኛ የግብርና ስራን በማዘመን ወጣቱን በማሳተፍ እድገቱ 11.1 በመቶ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ  በሪፖርታቸው ካካተቷቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የዋጋ ግሽበት አንዱ ሲሆን ባሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበቱ  7.2 በመቶ መድረሱን ተናግረው የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎችን  ግሽበት 7.4 በመቶ ለማድረስ ተሰርቶ 7.1 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

 

የሃገሪቱን የታክስ አሰባሰብ በተመለከተ  94.3 በመቶ ለመሰብሰብ ታቅዶ 92 በመቶ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 17 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡የመንግስት የፋይናንስ ጉድለት 2.5 በመቶ መድረሱን ተናግረው በ2010 ዓም በትላልቅ ግብር ከፋዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

 

 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በሪፖርተቸው መንግስት በቀጣዩ የስራ ዘመኑ የግብር ማጭበርበር እና የግብር ስወራን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፡፡ግብርን በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረተ እና ግብር ከፋዩን ያሳተፈ ስራ እንደሚሰራ ተናግረው የገቢ ሂሳብ ሳይዙ የሚሰሩትን ሂሳብ ኢንዲይዙ ለማድረግ ይሰራል፡፡ በዚህም ከግብር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንፈታለን ብለዋል፡፡

 

ባለፈው አመት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞን ነበር ያሉት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ የኤክስፖርት አቅምን በማሳደግ እየሰፋ የመጣውን የውጭ ንግድ ልዩነት በማጥበብ ይሰራል በተለይም እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ አበባ ልማት እና ቅመማ ቅመም ያሉ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጠንም በጥራትም ለማሳደግ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት በጥናት ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ይደረጋል ብለዋል፡፡

 

ቁጠባን  ለማበረታታት የፋይናንስ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ለሁለቱ ምክርቤቶች የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ 23 በመቶ የባንክ ተቀማጭ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ይህም የባንኮችን ቅርንጫፍ በማስፋት የተገኘ ነው ብለውታል በዚህም መሰረት ቁጠባ 29 በመቶ እንዲያድግ ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

አምራች ዘርፉን በማሳደግ የሰብል ምርት እድገትን ለማምጣት የግብርና ሜካናይዜሽን ስራን በመስራት አስፈላጊ እና ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን የማሰራጨት ስራ  ይሰራል፡፡

መሰረተ ልማትን በተመለከተ 75 በመቶ የገጠር መንገድ ተደራሽ በማድረግ ቀበሌን ከቀበሌ ማገናኘት ተችሏል፡፡

 

በዚህ ዘርፍ በትላልቅ መንገዶች ላይ 8 ፕሮጀክቶች ኮንትራክተሮቹ በማዘግየታቸው እና አንዳንድ ችግሮችን በመፍጠራቸው ምክንያት አቋርጠው እንዲወጡ እና በሌሎች ኮንትራክተሮች እንዲተኩ የማድረግ ስራ ለመስራት እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡

የባቡር መንገድን በተመለከተ የአዲስ አበባ- ጅቡቲ የባቡር መስመርን አገልግሎት የማስጀመር እና በግንባታ ላይ ያሉትን የማስጨረስ ስራ የሚሰራ ሲሆን በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ግን ዘንድሮ አዲስ የምንጀምረው ስራ አይኖርም ነው ያሉት፡፡

 

የኤሌክትሪክ ሳብስቴሽንን በተመለከተ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የታዳሽ ሃይልን በማስፋፋት የገጠሩን ማህበረሰብ የሃይል አቅርቦት እንዲያገኝ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የቴክኒክ ተቋማትን  በሁሉም ወረዳዎች በማስፋፋት እና የዩኒቨርሲቲዎችን የላብራቶሪ መሳሪያ በማሟላት የትምህርት ጥራትን እናመጣለን ያሉት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል እና የዲሲፕሊን ሁኔታን እና የስነ ዜጋ እና የስነምግባር ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት እንደሚሰጥ አስምረውበታል፡፡

 

በጤናው ዘርፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል እና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እና መድሃኒት አቅርቦትን ማሻሻል ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይገኛሉ ብለዋል ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሸመ፡፡

ሙስናን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በመናገር የሪፎርም ስራን ውጤታማ በሆነ መንገድ የማስተግበሩ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን አካል እንዲቆጣጠር የማድረግ አቅሙ እንዲጎለብት ስራ እንደሚሰራ እና  ከፖለቱካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ድርድር በዓመቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ለልማት ማሳለጫ ትልቅ መሳሪያ የሆኑትን ሚዲያዎች የጋራ ፎረም እንዲመሰርቱ ማድረግ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

ፕሬዝዳንቱ  በሪፖርታቸው ያካተቱት ሌላው ጉዳይ የስራ እድል ፈጠራን የተመለከተ ሲሆን በፌደራል ደረጃ 10 ቢሊየን በክልል ደረጃ 10 ቢሊየን በድምሩ 20 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ መዘግየቱ እንዳለ ሆኖ እስካሁን 2 ሚሊየን ወጣቶች ስራ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙትኝ ቀሪ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ ስራ  በቀጣይ  ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ ለምክርቤቶቹ መልካም የስራ ዘመን በመመኘት ንግግራቸውን አጠናቀዋል ፡፡ 

 

ሪፖርተር፡-ምስጋናው ብርሃኔ

  

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3527322
  • Unique Visitors: 199328
  • Published Nodes: 2627
  • Since: 03/23/2016 - 08:03