በኢትዮጵያ የሚሰጡ ወታደራዊ ስልጠናዎች ለተለያዩ አገሮች ወታደራዊ አታሼዎች አቅም እየፈጠሩ ነው

ባህር ዳር፡ መስከረም 30/2010 ዓ/ም (አብመድ)በኢትዮጵያ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስልጠናዎች ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ተለያዩ አገሮች ለሚሰማሩ ወታደራዊ አታሼዎች ተጨማሪ አቅም እየፈጠሩ መሆኑ ተነገረ።

Image may contain: one or more people and outdoor

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከጄኔቭ የደህንነት ፖሊሲ ማዕከል ጋር በመተባበር ለተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ለ6ኛ ጊዜ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገሮች የሠላም አስከባሪ ወታደሮችን በማሰማራት ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ያላት ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በዚህም በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ 12 ሺህ 553 እንዲሁም በግል 250 የሠላም አስከባሪ ባለሙያዎችን በማሰማራት ግንባር ቀደም የሠላም ዘብ መሆኗን እያስመሰከረች ነው።

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሃብታሙ ጥላሁን እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በመስጠት በአህጉሪቱ 'የልህቀት ማዕከል' እየሆነ መጥቷል።

ስልጠናዎቹ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገራት ለምታሰማራቸው የሠላም አስከባሪ ባለሙያዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተጨማሪ ልምድና አቅም እንድትፈጥር እያገዟት መሆኑንም አዛዡ ተናግረዋል።

ኢዜአ በላከው መረጃ ኢትዮጵያ የካበተ ወታደራዊ ልምድና እውቀት ካላቸው አገራት ጋር በቅርበት መስራት የምትችልበትንም ዕድል ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ሃብታሙ።

በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ዳንኤል ሁን በበኩላቸው በአገሮች መካከል የሚደረጉ ወታደራዊ ስልጠናዎች የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር በምታከናውናቸው ዓለምአቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውጤታማ እንደሆነች ጠቅሰው፤ የሠላም አስከባሪ ኃይሏም የዚህ ስልጠና ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል።

የአካባቢዋን አገሮች ደህንነት በመጠበቅና በአካባቢው ሠላም በማስፈን እያበረከተችው ስላለው የጎላ አስተዋፅኦም አውስተዋል አምባሳደሩ።

የጄኔቫ የደህንነት ፖሊሲ ማዕከል ወታደራዊ አማካሪ አንድሪያስ ቦልስተርሊ በበኩላቸው አገሮች በቅንጅት ሲሰሩ ሠላምና ፀጥታን የሚያደፈርሱ ጉዳዮችን በቀላሉ ማክሸፍ ይችላሉ ብለዋል።

ዓለማቀፋዊ ወታደራዊ ስልጠናዎችም የተለያዩ አገሮችን ልምድ በማጋራት የደህንነት ኃይሉን ማጠናከር እንደሚያስችሉ ጠቁመዋል።

የጄኔቫ የደህንነት ፖሊሲ ማዕከል ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ጋር በቀጣይነት መስራት እንደሚፈልግም አመልክተዋል።

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3433591
  • Unique Visitors: 194891
  • Published Nodes: 2605
  • Since: 03/23/2016 - 08:03