በባህር ዳር ከተማ የፕላን ህግ እየጣሱ የሚሰሩ ነጋዴዎች ተበራክተዋል

ባህርዳር፡ጥር 25/2010 ዓ/ም(አብመድ)በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በዋና ዋና የከተማ መንገዶች ዳርቻ ለእግረኛና ለአረንጓዴ ልማት ተብለው በተከለሉ ቦታዎች ላይ የፕላን ህግ እየጣሱ የሚሰሩ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡Image may contain: sky, outdoor and nature

"ከተማ አስተዳደሩ ለአረንጓዴ ልማት ቦታዎች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ ቦታዎቹ በህገ ወጥ ነጋዴዎች እየተወረሩ ነው" የሚሉት ነዋሪዎች፣ ከተማ አስተዳደሩ ችግሩ ሲፈጠር እያየ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱን ኮንነዋል፡፡

ችግሩ የከተማዋን ገጽታ ክፉኛ ከማበላሸቱም ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

"ከከተማዋ የመንገድ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እኩል እያደገ ያለው ህገወጥ ንግድ ያሳስበኛል" የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ አቶ በቃሉ አለነ ዋና ዋና የሚባሉት የከተማዋ የመንገድ ዳርቻዎች በላስቲክ በረንዳ ወደ ስጋና መጠጥ ቤት ስለመለወጣቸው ይመሰክራሉ፡፡

"ሁኔታው 'መንግሥት የለም እንዴ!' ያስብላል›› የሚሉት አቶ በቃሉ ለአረንጓዴ ልማት ተብሎ የተለየውን ቦታ ለምን ወደተዘጋጀለት ጥቅም መቀየር እንዳልተቻለ ይተቻሉ፡፡

በባህር ዳር ከተማ ከጊዮርጊስ አደባባይ እስከ ከብት ገበያ፣ ከፓፒረስ ሆቴል እስከ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ህንጻ፣ ከጅንአድ እስከ አዲሱ ስታዲዬም፣ ከአባይ ማዶ ወደ ዲያስፖራ መገንጠያ እንዲሁም በተለያዩ አዳዲስ በተከፈቱ መንገዶች ግራና ቀኝ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ቦታዎች በህገወጥ መልኩ ለንግድ እየዋሉ የሚገኙ ስፍራዎች ናቸው፡፡

በአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተማ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሷሊህ አቡ እንደሚሉት በአንዳንድ የከተማዋ ቦታዎች ላይ የሚታየው አገልግሎት ለቦታው የማይመጥን እንዲሁም ፕላን ላይ የተቀመጠውን አሠራርና ሳይንስን የተከተለ አይደለም፡፡ በተጨማሪም አንዱ አገልግሎት ከሌላው ጋር አብሮ የማይሄድና ለደህንነትም አስጊ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡ ከችግሩ አንፃር እየተወሰደ ያለው ቁጥጥርም ደካማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በሠራቸው ተከታታይ ዘገባዎች ለውጥ አለመታየቱን አረጋግጧል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታትም የችግሩ ስፋት እያደገ መጥቷል፡፡

ይሁን እንጅ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላክ ዓለሙ ችግሩ ይህን ያህል አስከፊ ስለመሆኑ እውቅና የለኝም ይላሉ፡፡

"የከተማ ፕላን ህግ እየጣሰ የሚሠራ ነጋዴ ካለ መጠየቅ አለበት" የሚሉት አቶ መላክ ለሚፈጠሩ ስህተቶች ክፍለ ከተማውና ደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ብለዋል፡፡

አብርሃም አዳሙ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3884841
  • Unique Visitors: 215544
  • Published Nodes: 2870
  • Since: 03/23/2016 - 08:03