ሶማሊያ ሙስና ከተንሰራፋባቸው የዓለም ሃገራት ቅድሚያ ትወስዳለች፡- የተባበሩት መንግስታት.

ባህርዳር፡ጥር 25/2010 ዓ/ም(አብመድ)

ሶማሊያ ሙስና የተንሰራፋባት ሃገር በመሆኗ ለጦር ኃይሏ የምትሰጠውን እርዳታ እንደምትቀንስ አሜሪካ ባለፈው ታህሳስ ወር ማስታወቋን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃገሪቱ አሳሳቢ በሆነ ሙስና ውስጥ መውደቋን አረጋግጫለው ብሏል ፡፡

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ከሆነ ላለፉት አስርት አመታት ለሶማሊያ የሚሰጠው እርዳታ ለታለመለት አላማ ከመዋል ይልቅ ወደግለሰቦች ኪስ እንደሚገባ በጥናት ማረጋገጡን ተናግሯል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሶማሊያ ልዩ መልክተኛ ለአመታት የሰሩትን ጥናት አገባደው በሰጡት ሪፖርት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሃገሪቱ የታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም በአመራሩ ውስጥ ሙስና መስፋፋቱ በመንግስት ግንባታ ላይ እንቅፋት እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

የሶማሊያ አስተዳደር አለመረጋጋት ለሙስና መስፋፋት እንደምክንያትነት የጠቀሱት ጥናት አቅራቢው የሙስና ወንጀልን ለመግታት እና ለማስወገድ ይቻል ዘንድ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለመመስረት ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ምንም ዓይነት ውጤት አላስገኘም ብለዋል፡፡

"ሙስናን ያለፉት እና አሁን ያለው መንግስት ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የሙስና ትግሉ ከሙስና ባልጠሩ ሰዎች አማካኝነት የሚፈጸም በመሆኑ የሚፈለገውን ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም ››ብለዋል የፖለቲካ ተንታኙ ሃሰን ሼክ ኢማም፡፡

ሼክ ኢማም እንደሚሉት ከሆነ ‹‹ሙስናን ለመታገል የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑም በላይ ሙስናን ለመዋጋት የሚያስፈልጓት ተቋማት እና ስልቶች የላትም›› ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ ትልቅ ክፍተት መኖሩን የሚናገሩት ሼክ ኢማም ‹‹እኛ ትክክለኛና ተግባራዊ የሆነ የፍትህ ስርዓት መገንባትና የሚቋቋሙትም የፀረ-ሙስና ድርጅቶች ከየትኛውም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቶች ነጻ ሊሆኑ ይገባቸዋል ›› ብለዋል፡፡

ይህ ሲሆን ብቻ ነው መንግሥት ሙስናን በትክክለኛው የለውጥ ሰራዊት አማካኘነት መዋጋት እና ተልዕኮውን በድል መወጣት የሚያስችለው ብለዋል ሮይተርስ እንደዘገበው፡፡

በቦታው ላንቺ ተረፈ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3870420
  • Unique Visitors: 214842
  • Published Nodes: 2859
  • Since: 03/23/2016 - 08:03