ህብረተሰቡ ወሳኝ ኩነቶችን እያስመዘገበ አይደለም

ባህርዳር፡ጥር 25/2010 ዓ/ም(አብመድ)ተፈጥሯዊ የሆኑትን ልደትና ሞትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ወሳኝ ኩነቶችን እንዲመዘግብ የተቋቋመዉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ እንደገለፀዉ ህብረተሰቡ ጉዳዩን በቸልታ ስለሚያየዉ ተግባሩ የሚጠበቀዉን ያህል አልሆነም፡፡

ሆኖም በባህርዳር ከተማ አሰተዳደር የጣና ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ወርቅነሽ አዝዘዉ እንደገለጹት ህብረተሰቡ በመመዝገቡ ወዲያዉኑ የሚያገኘዉ ጥቅም ወይም አገልግሎት እስከሌለ ድረስ ሀገራዊ ፋይዳዉን ተረድቶ እየተመዘገበ አይደለም፡፡

የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት የጽህፈት ቤቱ እቅድና ክንዉን ሲታይ ከሀምሳ ሺህ በላይ ህዝብ በሚኖራባቸዉ ሁለት ቀበሌዎች ከ1200 በላይ ልደት ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት ሰባ ጨቅላ ህጻናት ብቻ ናቸዉ፡፡

ጋብቻን በተመለከተም 250 ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገበዉ 30 ፤ ሞትን በተመ ለከትም ከ300 በላይ ታቅዶ የተመዘገበዉ አንድ ሰዉ በተመሳሳይ ፍቺን በተመለከተ ስልሳ አንድ ታቅዶ አስራ ስምንት ሰዎች ብቻ ወቅቱን ጠብቀዉ መመዝገባቸዉን አስተባባሪዋ ተናግረዋል፡፡
እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ ከህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ በተጨማሪ ምዝገባዉ የታደሰ መታወቂያ መጠየቁ፣ ለልደት ደግሞ እናትና አባት አብረዉ እንዲገኙ መመሪያዉ ማስገደዱ ለቁጥሩ መቀነስ የራሳቸዉን አስተዋጾ አድርገዋል፡፡

ምዝገባዉ በክልል በሚገኙ አስራ ሶስት ዞኖች ፣ አንድ መቶ አስራ ስድስት ወረዳዎች፣ሰላሳ አንድ ክፍለ ከተሞች እና በሜትሮፖሊታን ከተሞች በአጠቃላይ በ31 ሺህ አምሳ አንድ ቀበሌዎች ላይ ምዝገባ እንደተጀመረ የገለጹት ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አረጋ ከበደ ናቸዉ፡፡

በገጠር አካባቢዎች ከተሞች የተሻለ አፈፃፀም እንዳለም ተናግረዋል፡፡ በከተሞች ለታየዉ አፈጻጸም ዝቅተኝነት ስራዉን የሚአካሂዱት በከተሞች ከንቲባዎች ፤ በቀበሌዎች ደግሞ ስራ አስኪያጆች መሆናቸዉና ስራዉን በሀላፊነት አለመወጣታቸዉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የክትትልና ድጋፍ ስራዉ ደካማ መሆኑንም ለዉጤቱ አነስተኛነት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጨምረዉ አብራርተዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተደነገገዉና ለማንኛዉም ሀገራዊ ጉዳይ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለዉ የሚገለፀዉ የወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል መተግበር የጀመረዉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ነዉ፡፡


ጥላሁን ቸሬ

Image: 

Visitors

  • Total Visitors: 3300966
  • Unique Visitors: 189355
  • Published Nodes: 2588
  • Since: 03/23/2016 - 08:03